Monday, December 4, 2017

ቺምፕያ ሪፐብሊክ

በኬንያና ኡጋንዳ አዋሳኝ ድንበር ላይ ታይቶ የማይታወቅ ነገር ተከሰተ። ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ አልጄዚራ የሙሉ ቀን ሰበር ዜናቸው ይኸው ክስተት ሆነ። ፕሬዚደንት ትራምፕ ጉዳዩን አጣርቶ አስቸኳይ እርምጃ የሚወስድ ኮማንድ ፖስት አቋቋሙ። የሲአይኤ ሰው አልባ አውሮጵላኖች በአፍሪካ ሰማይ ላይ ይራወጡ ጀመር። የመላው ዓለም ዓይን ምሥራቅ አፍሪቃ ላይ አፈጠጠ።

ኦክቶበር 20, 2018 በኬንያ እና ኡጋንዳ ድንበር ላይ የሚገኙ የቺምፓንዚ ዝርያዎችን ለማጥናት የተላኩ 15 የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው የናሽናል ጄኦግራፊ አጥኚ ቡድን አባላት ባልታወቁ አካላት ተገደሉ። የእነርሱን ገዳዮች አድመው ለመያዝ የተላኩት የኬንያና የኡጋንዳ የሠለጠኑ ፖሊስ አካላትም በዚያው ቀልጠው ቀሩ። የሲአይኤ የስለላ አውሮጵላኖች ያነሱት ፎቶግራፍ እንደሚያመለክተው ሁሉም ሟቾች  በጦር ተወግተው ነው የሞቱት።

የሰዎቹን አስከሬን ለማምጣት የተላኩት ሄሊኮፕተሮች ከአንዱ በስተቀር እንደጥይት በሚወናጨፉ ግዙፍ ድንጋዮች ተመትተው ወደቁ። የአንዱ ሄሊኮፕተር አብራሪ አስከሬን ለማንሳት በወረወረው መንጠቆ ሰዎቹ ከተገደሉበት ጦር አንዱን ይዞ ተመለሰ። በዓለም የታወቁ ሳይንቲስቶች ጦሩን እንደነጠረ ማዕድን ከበው መረመሩት። የጦሩ ጫፍ በደም ውስጥ በፍጥነት በመሰራጨት ገዳይ የሆነ መርዝ ተቀብቷል። መርዙ ሁለት በምሥራቅ አፍሪካ ሳቫና ብቻ የሚገኙ የዛፍ ቅጠሎችን ቀይጦ በመጨቅጨቅ እንደሚዘጋጅ ለማረጋገጥ ሳይንቲስቶቹ ግዜ አልፈጀባቸውም።

ይህ በእንዲህ እያለ በግዙፍ ድንጋይ ወንጭፍ እየተመቱ ከወደቁት የሲአይኤ ድሮኖች መካከል አንዷ ከወደቀችም በኋላ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን መላኳን ቀጥላለች። የተማረከችው ድሮን መንቀሳቀሷን ቀጥላለች። ተንቀሳቃሽ ምስሉ የሚደርሳቸው ሰዎች ድሮኗን የማረኳት አካላት እየተቀባበሉ እየተመለከቷት መሆኑን ለማወቅ ብዙ አልተቸገሩም። ድሮኗ እየተመረመረች ነው። እሷም መረጃ መላኳን አላቋረጠችም። በምትልከው ምስል ውስጥ ከፍተኛ ጫጫታ ይሰማል። የሚያስደነግጠው ግን ሌላ ነው።

ብዙ በሁለት እግራቸው ቀጥ ብለው የሚረማመዱ ቺምፓንዚዎች ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ። በግዙፍ ድንጋይ የተገነቡ ምሽጎች አሉ። ሃምሳ ኪሎ የሚመዝኑ ድንጋዮችን እንደጠጠር የሚያፈናጥሩ መቀሰቻዎች ተተክለዋል። መቀሰቻዎቹን የፈረጠመ ጡንቻ ያላቸው ቺምፓንዚዎች ወጥረው በመያዝ በሰማያቸው ላይ የሚያንዣብቡትን ድሮኖች እንደበረዶ ያረግፏቸዋል። ሌሎች ቺምፓንዚዎች ተጠርበው አግድም እና ሽቅብ ከተከመሩት ድንጋዮች እያጋዙ መቀሰቻው ላይ ያስቀምጣሉ። ሌሎች ቺምፓንዚዎች ቅጠላ ቅጠሎችን በጥንቃቄ ከድንጋይ በተጠረበ ሙቀጫ ውስጥ ከድንጋይ በተሠራ ዘነዘና ይጨቀጭቃሉ። ትዕዛዝ የሚያስተላልፉ የሚመስሉ ቺምፓንዚዎችም በምስሉ ይታያሉ። ሁሉም ነገር በሥርዓቱ የታቀደ እና እየተካሔደ ያለ ይመስላል። ሲአይኤ የደረሰውን ምስል ‘ጥብቅ ምሥጢር’ ሆኖ እንዲያዝ ትዕዛዝ በአስተላለፈ 10 ደቂቃ ውስጥ ድሮኗ የምትልካቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች ተጠልፈው ባልታወቁ ሰዎች አማካይነት በኢንተርኔት በቀጥታ ተሰራጨ።

ዜናው በዓለምዐቀፍ ሚዲያዎች ሁሉ ሰበር ዜና ሁኖ ቀጠለ። የዓለም ሰዎች ሁሉ በፍርሐት ራዱ። ኡጋንዳ እና ኬንያ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አስተላለፉ። በምሥራቅ አፍሪካው ሳቫና ዙሪያ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ ያሉ ሰዎች በሙሉ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ በአስቸኳይ እንዲወጡ ታዘዘ። ከፍተኛ ግርግር ምሥራቅ አፍሪካን አመሳት። የቺምፓንዚዎች የተደራጀ መንግሥት መፈጠሩ ተረጋገጠ። ላለፉት በርካታ ምዕተ ዓመታት በዓለም ላይ ብቸኛው ፈላጭ ቆራጭ የነበረው የሰው ዘር ደነገጠ። የዜና አውታሮች አዲሱን የሰው ዘር ተቀናቃኝ አዲስ ግዛተ መንግሥት ‘ቺምፕያ ሪፐብሊክ’ ሲሉ ጠሩት። ቺምፕያ ሪፐብሊክ ከብዙ የዓለም አገራት ሥም ሁሉ ደምቆ የሁሉንም ሰው ጆሮ አንኳኳ። ፍርሐት በሰዎች ግዛት ነገሠ።

በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በአውሮጳ እና በአሜሪካ ሕዝባዊ ሰልፎች ቀለጡ። የኬንያ እና ኡጋንዳ መከላከያ ሠራዊቶች ለበርካታ ምዕተ ዓመታት የሰው ኮቴ ያልጎበኘውን ሳቫና በጦር ጀቶቻቸው ለመደብደብ ወሰኑ። በመጀመሪያው ነገሩን የማጣራት ሙከራ የደረሰውን የቁስ ኪሳራ በማስታወስ በቂ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ በማሳሰብ ሲአይኤ ውሳኔያቸውን አሰረዛቸው። ችምፓንዚዎቹ ምንያህል እንደተዘጋጁ አይታወቅም። የተማረከችው ድሮን ባፍጢሟ መሬት ከተደፋች በኋላ የምታስተላልፈው ጨለማ ብቻ ሆኗል።

ጊዜ በገፋ ቁጥር ዓለም በቺምፕያ ሪፐብሊክ ምክንያት ለሁለት ተከፈለች። የአፍሪካ እና የእስያ ሕዝቦች ቺምፓንዚዎቹ ከነመንግሥታቸው በአስቸኳይ እንዲደመስሱ መንግሥታቶቹን ማስጨነቅ በቀጠሉ ቁጥር፣ አውሮጳውያኑ እና አሜሪካውያኑ የተለየ ድምፅ ይዘው ብቅ አሉ። ‘ቺምፓንዚዎቹ የራቸውን መንግሥት የመመሥረት መብት አላቸው’ የሚሉ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች በሰሜን አሜሪካ፣ ለጥቁሮች መብት ንቅናቄ ከተደረገው ሰልፍ ወዲህ ትልቅ የሚባለውን ሰልፍ አካሔዱ። እነዚህ የቺምፕ ሪፐብሊክ ደጋፊዎች ‘ቺምፕስታ’ በሚል ሥም መጠራት ጀመሩ። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ‘ኮንቴይንመንት’ የተባለ ፖሊሲ በኮንግረሳቸው አፀደቁ። ዓላማቸው ለግዜው ቺምፕ ሪፐብሊክ ከመሥራቅ አፍሪካው ሳቫና እንዳይስፋፋ መመከት ብቻ ሆነ። በድጋሚ የተላከች ድሮን በድንጋይ ተመትታ ከመውደቋ በፊት፣ ሦስት ሜትር ርዝመት ባለው የድንጋይ ካብ የተገነባ አገር የሚያክል ምሽግ እንዳለ አረጋገጠች። አዲሱ ምስል ቺምፓንዚዎቹ ከሰዎች ጋር ጦርነት ለመግጠም ለረዥም ግዜ መዘጋጀታቸው አሳወቀ።

ምዕራቡ ዓለም በአዲስ የአፍሪካውያን ስደት ተመታ። የአፍሪካ ኅብረት ጥምር ሠራዊት የምሥራቅ አፍሪካውን ሳቫና ለመክበብ ኃይሉን ሁሉ ከሠላም ማስከበር ቀጠናዎች አውጥቶ ኬንያና ኡጋንዳ ላይ አሰፈረ። የዳርፉር፣ የኢትዮኤርትራ እና የሶማሊያን፣ ጨምሮ የሌሎቹም አካባቢዎች ግጭቶች አገረሹ። የዓለም የሰው ዘሮች አንድ ሆነው መቆም ባለባቸው ግዜ ተከፋፈሉ። የሰብኣዊ ቀውስ ተፈጠረ። የዓለም መንግሥታት ግን ከቺም ሪፐብሊክ በላይ አስፈሪ ፈተና አልገጠመኝም በሚል ትኩረት ነፍጎታል። የሰው ልጅ የዘመናት የበላይነት በምድር ለመጀመሪያ ግዜ በቺምፓንዚዎች መፈተኑ ያልታሰበ ፍርሐት አጫረ። ሆኖም የምዕራብ መንግሥታት ከተለመደው በላይ በሆነው የሕዝቦቻቸው ጫና ወደቁ። ቺምፕስታዎች በምዕራብ አገራት ዋና ዋና ከተሞች ሁሉ በአንድ ቀን የጠሩት ሰልፍ ምዕራቡን የዓለም ክፍል በድጋሚ ሲንጠው ዋለ። “ዓለም ለሰው ዘር ብቻ አልተፈጠረችም”፣ “አምላክ በዓለም ላይ ያነገሠውን መቀበል አለብን”፣ “ዓለምን ለሰው ዘር ብቻ ማመቻቸት ዘረኝነት ነው” የሚሉ መፈክሮች በሃይማኖተኞች ሳይቀሩ ተንፀባረቁ።

ውጥረት ውስጥ የገቡት ኃያላን መንግሥታት ረቂቅ ስምምነት አዘጋጁ። ስምምነቱ የፕሬዚደንት ትራምፕን የኮንቴይንመንት ፖሊሲ መሠረት ያደረገ ነው። በምሥራቅ አፍሪካው ሳቫና ያለውን 400 ኪሎ ሜትር ስኩዌር መሬት የቺምፕ ሪፐብሊክ እንደሆነ በመቀበል፣ በኮንቴይንመንት ፖሊሲ መሠረት እንዳይስፋፋ ዙሪያውን ማጠር የሚል ስትራቴጂ ይዟል። ቺምፕስታዎች አጥር መታጠሩ የቺምፓንዚዎቹን የመንቀሳቀስ እና የመስፋፋት ተፈጥሯዊ መብት ያግዳል ብለው በፅኑ ተቃወሙት። የሆነ ሆኖ ዩ ኤስ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ስዊድን ስምምነቱን በፍጥነት አፀደቁት። የአፍሪቃ ሕዝቦች ስምምነቱን በዓለም ታሪክ አውሮጳውያን አፍሪቃን ለመቀራመት ካደረጉት ስምምነት ወዲህ ትልቁ የአፍሪካን ሉአላዊነት የተጋፋ ስምምነት ነው ብለው አወገዙት። ለኮንቴይንመንት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የተበጀተው ረብጣ ያስጎመጃቸው ብዙዎቹ የአፍሪካ መንግሥታት ግን የምዕራብውያኑን ስምምነት ወዲያው ተቀብለው አፀደቁት።

የኬንያ እና የኡጋንዳ መንግሥታት ግን ከመሬታቸው ተቆርሶ ለቺምፕ ሪፐብሊክ መሰጠቱን አንቀበልም አሉ። ተመራማሪዎች ከመገደላቸው በፊት ምን እየተካሔደበት እንደነበር የማያውቁትን ግዛታቸውን ለማስከበር ጦራቸውን ሰብቀው ተዘጋጁ። ብዙ የአፍሪካ አገራት ሕዝቦች፣ የየራሳቸውን መንግሥት ውሳኔ ሽረው ከኬንያ እና ከኡጋንዳ መንግሥታት ጋር ተሰለፉ። ዓለም በሁለት ፈርጅ ለጦርነት ተዘጋጀች፤ የቺምፕ ሪፐብሊክን በሚደግፉ እና በሚቃወሙ የሰው ልጆች መካከል ፍጥጫ ሆነ። ሰዎች የቺምፕ ሪፐብሊክን ዘንግተው ሌሎች የሰው ዘሮች ላይ አተኮሩ።

አፍሪቃውያን ምዕራባውያን ላይ አመፁ። ምሥራቃውያን ተደረቡላቸው። የሰው ዘሮች በቺምፓንዚ ዘሮች ኅልውና ላይ መስማማት ባለመቻላቸው ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ተጀመረ። 

3 comments:

  1. ፅሁፉን አንብቦ ለመጨረስ ከፈጀብኝ ጊዜ ይልቅ የላይክ ቦታውን ስፈልግ ያጠፋሁት ጊዜ ሌላ ሶስት ፅሁፍ ያስነብበኝ ነበረ።
    ጥሩ ምናባዊ ፈጠራ ነው። ኬንያ ስላለሁኝ እስከ ግማሽ ድረስ ልቤ እየመታ ነው ያነበብኩት...

    ReplyDelete