Thursday, October 13, 2016

ፍቅረኛዬን ያያችሁየቀድሞ ፍቅረኛዬን - ሊሊን ካያችሁ - ውበት አይታችኋል። ሊሊን የጠበስኳት በገጣሚ ግሩም በለጠ ግጥሞች ነው። ግሩም አገር ያወቀው፣ ሊቅ ያደነቀው ገጣሚ አልነበረም። መጀመሪያ እኔ ብቻ ነበርኩ የማደንቀው። በኋላ ሊሊም ተጨመረችለት። የቀድሞ ፍቅረኛዬ ሊሊ ደግሞ ሙገሳ ስትወድ አይጣል ነው። ለነገሩ በኋላ ላይ ይበልጥ ሳውቃት ቁንጅናዋ ሙገሳ አይመጥነውም። እናም የመጀመሪያ ቀን የተዋወቅኳት የግጥምን በጃዝ ምሽት ላይ ነበር። ጎን ለጎን ተቀምጠን በጨዋታ ተግባባን። ዝግጅቱ አልቆ ስንወጣ ብሸኛት ትፈቅድ እንደሆን ጠየቅኳት እና ተስማማች። የግጥም ምሽት ላይ ስላገኘኋት በምትወደው ነገር ልቀላጠፋት ብዬ ስለግጥም ሳወራላት ቆየሁ።

“ግሩም በለጠን ታውቂዋለሽ?” አልኳት፤ አታውቀውም።

አንድ ግጥሙን በቃሌ ወጣሁላት፦

“በተውሶ ብርሃኗ፥  እንዳላደነቅኳት፣
ዓይንሽን አይቼ፥  ጨረቃዋን ናቅኳት።
በነጋ በጠባ፥ ደጁን እንዳልሳምኩኝ፣
ከንፈርሽን ቀምሼ፥ ሃይማኖቴን ተውኩኝ።
እንዲህ፣ እንዲህ እያልኩ፥ በተራ፣ በተራ፣
የቀድሞ ልማዴን፥ ሜዳ ላይ ስዘራ፣
ካንቺጋ መሆንን እንደስኬት ጣሪያ
ለጋ ከን‘ፈርሽን፣ ቀን ቀን ለመዋያ፣
እግርሽ መሐል ካለው፣ ማታ መቀበሪያ፣
ይሁነኝ እያልኩኝ፥ ሁሌ እባክናለሁ፣
በከንፈርሽ ስመሽ፣ ግደይኝ ብያለሁ፣
ውስጥሽ ለመቀበር፣ ሞትን እንቃለሁ…"

በጣም አሳቃት፤ “የግሩምን ግጥሞች የት አገኛቸዋለሁ?” አለችኝ።

ወቅቱን የጠበቀ ጥያቄ ስለነበር ደስ አለኝ። “ገበያ ውስጥ ያለ አይመስለኝም፤” አልኳት “እኔጋ ስላለ አውስሻለሁ።” የግሩምን ግጥሞች በቃሌ ስለማውቃቸው ብሰጣት የሚጎድልብኝ ነገር ያለ አይመስለኝም። ነገር ግን ሊሊን ደጋግሞ ለማግኘት፣ መጀመሪያ ለማዋስ፣ ቀጥሎ ለማስመለስ፣ ሠልሶ ቦርሳዋ ውስጥ ረስታው የሔደችውን መጽሐፍ ድጋሚ ለማስመጣት፣ በመጨረሻም አብሮ ተኝቶ ለመንቃት የነበረኝ አማራጭ ይኸው ብቻ ነው። ጀንጃኝ የምባል ዓይነት ወንድ አይደለሁም። ነገር ግን ዕድሉን ሳገኝ መጀመሪያ ቀልብ፣ ከዛ ሌላ ነገር የሚያቀልጥ ምላስ እንዳለኝ አውቃለሁ።

“በጣም ደስ ይለኛል” አለችኝ። ከሊሊ ጋር ስልክ መቀያየር በጣም ቀላል ነገር ሆነ። በማግስቱ ተገናኘን።

ውበቷ ትላንት ካየሁት ብሶበታል። ምናልባት አብሳበት ነው የመጣችው። "አብሺው፣ አብሺው፣ አባብሺው" አደል የሚለው ዘፋኙ?! ከንፈሯን በቀይ ቀለም አስጊጣ ዳር ዳሩን በጥቁር ቀለም አጥራዋለች። ወንድ ልጅ ለማማለል የተሳለ ስዕል እንጂ ከንፈር አይመስልም ነበር። አይኗ እንኳንስ ተኩሎ ወትሮም እዩኝ እዩኝ የሚል ዓይነት ነው። በዛ ላይ የሸሚዟ ሁለት ቁልፎች አልተቆለፉም። በዚያ ላይ አጭር ቀሚስ ነው የለበሰችው።

"የግሩምን ግጥሞች እንዴት አገኘሻቸው?" አልኳት በውበቷ እየተገረምኩ እንዳልተገረምኩ ለማስመሰል።

"መቼ አንብቤያቸው?" አለችኝ ሳቅ ውስጡ ባዘለ የሚፍለቀለቅ ድምፅ። ያንት ያለህ! ለካስ ዛሬ ገና ነው የማውሳት። ውበቷ እግዜር ካለ የሚያዳላ እግዜር መኖሩን ያረጋግጣል። ብዙ ሴቶች በድካም የማያገኙትን ስኬት በጥቅሻ እንደምታገኘው ለማወቅ ደቂቃ አልፈጀብኝም። የራሴን ስሜት አውቀዋለኋ! አሁን እንዲህ ተውባ መጥታ ነፍሴን ብትጠይቀኝ እንዴት አስችሎኝ እከለክላታለሁ?!

"የክሊዮፓትራ፣
ያ ሰልካካ አፍንጫ፣
እንዲያ ተገትሮ
ባይፈጠር ኑሮ
የዓለም ካርታ እንዳሁን፣
አይሆንም ነበረ፣
ብሎ ያለው ማነው?
እኔ አልፈርድበትም፣
አንቺን ባያይሽ ነው!”

"ውይ ደስ የሚል ግጥም፣ የማነው?" አለችኝ። "አሁንም የግሩም ነው እንዳትለኝ?"

“አዎ፣ የግሩም ነው” አልኳት። ግሩም ሊሊን አንድ ቀን አይቷት መሆን አለበት ግጥሞቹን የጻፋቸው ብዬ አሰብኩ። የውበቷ ምሥጢር ምንድነው ብዬ ማሰቤን አልዋሽም። አንዳንዴ በጣም ቆንጆ መስለው የሚታዩኝ ሴቶች ያልቀመስኳቸው ናቸው፤ የሊሊ ግን የተለየ ነበር። ሰልቅጬ ብበላት እንኳን አልጠግባትም። መቅናት ጀመርኩ። ወዲያው። ሌሎች ወንዶች እግሯን፣ ከሸሚዝ ከለላ የተረፈውን ደረቷን፣ ዓይኗንና ከንፈሯን እንደሚያዩት እና እንደሚመኙት ሳስብ ቀናሁ። በቅፅበት ቦዲ ጋርዷ መሆን ተመኘሁ። ከወንዶች ዓይን ስጠብቃት ልውል አሰኘኝ።

የግሩምን ግጥሞች እየገላለጥኩ ሳነብላት። እሷ ስትስቅልኝ አመሻሽተን ተለያየን። በርግጥ ተለያየን ማለት ይከብዳል። ሸኝቻት እቤቷ ስትገባ በድብቅ፣ በልቤ ተከትያታለሁ። በስውር ቦርሳዋን ሶፋ ላይ ስትወረውር፣ ባለተረከዝ ጫማዋን ስታሽቀነጥር፣ ልብሷን አወላልቃ ስትታጠብ በምናቤ አይቻታለሁ። ለዚያ ነው የቤቴ መንገዱ ያጠረልኝ።

ሊሊን በየቀኑ አገኛት ጀመር። "አይመቸኝም" ብላኝ አለማወቋ አንድ ርምጃ፣ ለወሬዬ ያላት አድናቆት እና በሳቅ የታጀበ ምላሽ ሁለት እርምጃ አደፋፍሮኝ አንድ ቀን ደጃፏ ላይ ከንፈሯን ሳምኳት። ስንት ሰከንድ፣ ደቂቃ፣ ወይም ዓመት እንደሳምኳት አላውቅም። ሰውነቴ ለፍልሜያ እንደተዘጋጀ ነብር ተነፋ። ብቻ ከዚያ በኋላ ሠርግና ምላሽ ሆነ። ሊሊ ስስት አታውቅም። ፍቅር ያለስስት ሰጠችኝ። እውነትም ደግሞ ለምን ትሰስታለች? ማታ ተኝተን ጥዋት ስንነሳ ውበቷ ጨምሮ እንጂ ባለበት እንኳ አግኝቼው አላውቅም። ግን እንደሳምኳት፣ እንደኮረሸምኳት፣ እንደመጠጥኳት ቶሎ ልጠግባት አልቻልኩም። እሷ ግን ቀድማ ጠገበችኝ። መሰለኝ። ታወቀኝ። በሕይወቴ የተሸነፍኩት፣ የመኖሬን ትርጉም ያጣሁት እሷ እንደጠገበችኝ ያወቅኩ‘ለታ ነው። ለኔ ሕይወት በሁለት ትከፈላለች፤ እሷን ከመውደዴ በፊት እና እሷን ከወደድኩ በኋላ።

አንድ ቀን፣ ሊሊ ከሜዳ ተነስታ "ይህንን ነገር ማቆም አለብን" አለችኝ። “ምኑን? ይሄንን?" አልኳት በጣቴ ወደታች እየጠቆምኩ። ሳቋን ለማየት ፈልጌ ነበር። አላሳየችኝም። የዛን ዕለት ቆንጆ ሴትም መኮሳተር እንደምትችል አሳየችኝ። ክፋቱ፣ ስትኮሳተርም ታምራለች። ምናለ ስንጣላ እንኳ አባርሮ የሚያስቀረኝ ገጽታ ቢኖራት?

"ፍቅረኛ አለኝ" አለችኝ። እንደፈራሁት። "ውጪ አገር ነው። ብቸኝነት ይሰማኝ ነበር። አንተን ሳገኝህ ልታመንለት አልቻልኩም" አለችኝ።

"እና አሁን ምን ተፈጠረ?" አልኳት።

"ፀፀቱን አልቻልኩትም" አለችኝ።

"ተዪው!" አልኳት። "አንቺን የመሰለች ውብ ጽጌረዳ፣ ማንም ሊቀጥፍበት እንደማይችል ትቶሽ ውጪ ከከረመ፣ አትገቢውም ተዪው!" አልኳት ቆፍጠን ብዬ። የግሩም ግጥም ትዝ እያለኝ፣

"ጽጌረዳ አበባ፣ ደጁ የተከለ
ቆንጆ ፍቅረኛውን፣ ከሰው ያልከለለ
ሁሉም ተታለለ።
የአላፊ አግዳሚውን፣ ልብ እያማለለ፣
ውሰዷት፣ ውሰዷት፣
ባለቤትም የላት፣ ቅጠፏት እያለ።"

"አልተወውም" አለችኝ። "ከውበቴ በላይ የሚመለከተኝ አንድ ሰው ቢኖር አልተወውም" አለችኝ። ስህተቴ ገባኝ። አላውቃትም ነበር፤ ውበቷን ከማድነቅ እና ከማድረቅ ውጪ ሌላ ነገሯን፣ ሕይወቷን ሁሉ አላውቀውም ነበር። ተለያየን። ከዚያ በኋላ አንድ ቀን መንገድ ላይ አየኋት። ከገጣሚ ግሩም በለጠ ጋር ነበረች። ግራ ገባኝ። ውጪ አገር የነበረው ፍቅረኛዋ እሱ እንዳልሆነ አውቃለሁ። ምክንያቱም ግሩም ውጪ አገር ኖሮ አያውቅም። በደንብ አውቀዋለሁ። የሆነ ነገር ትዝ አለኝ።

አንድ ቀን ሊሊ፣ "ግሩምን እኮ ተዋወቅኩት" ብላኝ ነበር።

"ኧረ?" አልኳት።

"ምን እንዳልኩት ታውቃለህ? ‘እንዴት እንዲህ ዓይነት ድንቅ ግጥሞች እየፃፍክ በጣም ዝነኛ አልሆንክም?’ ስለው ‘ብዙ ቆንጆ ሴቶች ግጥም አይወዱም። እኔ ደግሞ ግጥም የምጽፈው ግጥሜን ለማያነቡት ዓይነት ሴቶች ነው’ አለኝ።" ፍልቅልቅ የሚለው ሳቋ ሲከተል እኔ የሸሚዞቿን ቁልፎች እየፈታሁ ነበር።
አሁን ገባኝ። ሊሊ ውበቷን ትወደዋለች። እኔ ግን ውበቷን የማወድስበት ቃል አልነበረኝም፤ እሷን ለመጥበስ ቃላት የተዋስኩት ከግሩም ግጥሞች ነው። ግሩም ግን የሷን ውበት ለማድነቅ ቃላት ከሰው አይዋስም። የግሩምን ግጥሞች ያስተዋወቅኳት እኔ ነኝ፤ እኔ ግን ግሩምን ማስተዋወቅ እንጂ መተካት አልችልም። ዓለሜ ለሁለት ተከፈለች፤ ግሩምን በመምሰልና በመተካት መካከል።

ከዚያ በኋላ ብዙ ግጥሞች ጻፍኩ። ብዙ መድብሎች አሳተምኩ። ዝና ከቤቴ መጣ፣ ነጻነት በመስኮት ወጣ። አገሬው የኔን ግጥሞች ያውቃል። የግሩምን ግጥሞች ግን አያውቅም። አገሬው የኔን ግጥሞች ማወቁ ግን ሊሊን ከግሩም መልሶ ወደኔ አላመጣልኝም። ጋዜጠኞች ለገጣሚነት ያነሳሳኝ ምን እንደሆነ ይጠይቁኛል።

"የኔ ያልነበረ ቅኔ እየዘረፍኩኝ፣
ዜማ እያወረድኩኝ፣
ያፈራሁት ዝና፣
ያወረድኩት መና፣
እኔን ካልወሰደ፣
አንቺን ካላመጣ፣
መጻፉም ይቅርብኝ፣
በአፍንጫዬ ይውጣ።"

የመጨረሻ መድብሌ ላይ ያሳተምኩት የመጨረሻ ግጥሜ ነው።

1 comment:

  1. ዋው ፍቄ በጣም ደስ ይላል ተመችቶኛል ይመችህ!!!

    ReplyDelete