Monday, December 6, 2010

የመንግስት ሠራተኛው የፍቅር ቀጠሮ (የdating እንጉርጉሮ)


ዕለቱ ሕዳር 27 ነው፤ የደሞዝ ቀን፡፡ ኪሱ በመቶ ብሮች ታጭቋል፡፡ ማታ የራት ግብዣ አለበት፡፡ የራት ግብዣው አቅራቢ እሱ ነው፤ ተጋባዧ ሜላት፡፡ ለዚህ የራት ግብዣ ብዙ ተዘጋጅቷል፣ በጣም ጓጉቷል፣ እንቅልፍ አጥቷል - በአራት ነጥብ ጉዳዩን ለማሳጠር ያክል የማይሆነውን ሆኗል፡፡

ሜላትን የተዋወቃት በፌስቡክ ነው፡፡ የጓደኞቹ ጓደኛ ፎቶ ላይ ‘Tag’ ተደርጋ አያት፡፡ ሒደቱ ቀላል ነበር፡፡ በመጀመሪያ ፎቶዋን ወደደው፡፡ ከዚያ ‘ፕሮፋይሏን’ ጎበኘ እና ወደደላት፤ በተለይ ‘Single’ መሆኗ ተመቸው፡፡ ለፌስቡክ ጓደኝነት ጠየቃት ተቀበለችው፡፡ ፎቶዎቿን በሙሉ አየ - በቀኝም፣ በግራም፣ በፊትለፊትም፣ በኋላም የተነሳቻቸው ፎቶዎቿ ያምራሉ፡፡ ለፌስቡክ ተራ ጓደኝነት ያንስባታል ብሎ አስቦ ለሌላ ነገር አጫት፡፡ ያንን ሌላ ነገር ሳይነግራት ‘Chat’ ላይ እየጠበቀ ስትገባ ያዋራት ጀመር፡፡ ለነገሩ እሷም ‘easy going’ መሆኗ ተመችቶታል፤ አስፈርቶታልም፡፡ ‘easy going’ መሆኗ ለእሱ ብቻ ካልሆነስ? ደግሞም አይሆንም፡፡

እሱ የመንግስት ሰራተኛ ነው፡፡ 1,600 ብር ተከፋይ የወር ደሞዝተኛ፡፡ ለነገሩ ከዚህችው ላይ ታክስ፣ የጡረታ አበል ምናምን ሲቆራረጥ ከ1,400 ብር በላይ ጥቂት አሥር ብሮች ናቸው የሚተርፉት፡፡ ታክስ የሚባል ነገር ያበሳጨዋል፡፡ “ይቺም ገቢ ሁና በገቢ ታክስ እና በቫት ተቀነጣጥባ ታልቃለች” እያለ ያማርራል፡፡ ምናልባት ብዙ ከተወራለት የጥር ወር ደሞዝ ጭማሪ በኋላ ተስፋ ሰንቋል - በደሞዙ ማነስ ላይማረር፡፡ ስንት ቢጨመርለት እንደማይማረር ግን አስልቶ አያውቅም፣ ማስላትም አይፈልግም፡፡