Wednesday, March 5, 2014

አክቲቪስቱ (ክፍል ፩)


በአለንጋ ጣቶቿ ጥቅልል፣ ጥቅልል እያደረገች ስታባብላቸው የነበሩትን የፀጉሯን ዘለላዎች በቁጣ ወደኋላዋ አሽቀነጠረቻቸው፡፡

‹‹አንተ መቼም ሰው አትሆንም፤… ሰው ከማይሆን ሰውጋ ዕድሜዬን ማቃጠል የለብኝም፡፡››

ንግግሯ የእሳት አለንጋ መሰለው፡፡ ዓይኖቿ ግን የምላሷን ያክል አልደፈሩትም፡፡ የተናገረችውን ሁሉ የተናገረችው ጠረጴዛው ላይ ዓይኗን እያንከባለለች ነበር፡፡ ከዝምታ በላይ የሚናገረው ነገር አልነበረውም፡፡ እሱ መናገር የሚፈልገውን እሷ መስማት አትፈልግም፤ ስለዚህ ዝም አላት፡፡

‹‹እስኪ ባባቢ ሞት ስለወደፊቱም ሆነ በከንቱ ስላለፈው ጊዜ ትንሽ አይቆጭህም? እሺ ስለኔ እንኳን ትንሽ አታስብም?›› ጠየቀችው፤ ዝም አላት! በከንቱ የባከነ የምትለው እሱ በሕይወቴ ቁምነገር የሠራሁበት የሚለውን ጊዜ ነው፡፡

ብስጭቷን መቆጣጠር አቅቷት ብድግ አለች፡፡ ለብቻው አንድ ወንበር ይዞ የነበረውን ቦርሳዋን አፈፍ አድርጋ ንጥቅ፣ ንጥቅ እያለች ሄደች፡፡ ብዙ ጊዜ ሲጋጩ ተስፈንጥሮ መሄድ ልማዷ ነው፤ የዛሬው ግን የመጨረሻዋ መስሎታል፡፡ ‹ምናለ ስመሽኝ እንኳን ብትሄጂ› ሊላት ነበር - ግን ምላሱ ደርቆ ቀረ፡፡ የለበሰችው እንደሃጫ በረዶ የነጣ ሱሪዋ ጠይም ገላዋን ሙሉ ለሙሉ መደበቅ አልቻለም፡፡ በርምጃዋ ፍጥነት የተቆጣው ዳሌዋ መቀመጫዋን ሲነቀንቀው ከኋላዋ ተመለከታት፡፡ በደረጃው ቁልቁል ወርዳ ስትሰወር የጫማዋ ተረከዝ ‹ቀጭ፣ ቋ፣ ቀጭ፣ ቋ…› እያለ እየራቀ፣ እየራቀ ሲሄድ ይሰማ ነበር፡፡ ድምፁ እልም ካለ ወዲያም በሱ ምናብ ውስጥ ‹ቀጭ፣ ቋ፣ ቀጭ፣ ቋ…› ማለቱን ቀጥሏል፡፡

ከሦስት ወራት በኋላ

ላጤው አክቲቪስት የሥራ ባልደረባውን በቤቱ እያስተናገደ ነው፡፡ ምግብ ማብሰል ‹‹አቻ አይገኝልኝም›› እያለ ይፎክራል፤ በእርግጥም ችሎታው ያልተመሰከረለት ሼፍ ያሳክለዋል፡፡

ሽርጡን ወገቡ ላይ ሸብ አድርጎ የጠባብ መኝታ ቤቱን አንድ ጥግ የተዋሰችው ሲሊንደሩ ላይ የሚጠባብሳቸው ነገሮች ቤቱን በምግብ ጠረን አውደውታል፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልኩ በድንገት ሲጠራ በጆሮው እና በትከሻው መሐል ስልኩን ሸጉጦ እያወራ ሽርጉዱን ቀጠለ፡፡

‹‹አዎ የኔ ቆንጆ…››

‹‹ኖ፣ ኖ፣ ኖ… መጀመሪያ ትንሽ ስብሰባ ላይ ነበርኩ… በኋላ አይቼው ስደውልልሽ ቢዚ ሆነብኝና… በዛው ረሳሁት››

‹‹አይ እንደሱ’ኳ አይደለም፤ እያወቅሽኝ?››

‹‹እ… እ… ይኸውልሽ ቆንጆ… በኋላ ብደውልልሽ ይሻላል፡፡ አሁን I’m in the middle of something.››

ስልኩን ሲዘጋው እንግዳው፣ ‹‹ማናት ባክህ… እንዲህ የምታቆላምጣት?››

‹‹ኤክሴ ነች››

‹‹ኧረ ባክህ?!... ተለያይታችሁ እንዲህ ከተፎጋገራችሁ፣ አብራችሁ ብትሆኑማ ኖሮ እንዴት ልታወሩ ነበር?...››

‹‹አብረን ስንሆንማ ተቃራኒ ነው… መሐከላችን ሠላም አስከባሪ ከሌለ በቀር በሠላም ማውራት እንኳን አንችልም ነበር፡፡›› አለ አፉን በሹፈት ፈገግታ አፉን አጣሞ፡፡

እንግዳው የሆነ ቦታ የሚያውቀው ታሪክ የተነገረው ይመስል ‹‹ለምንድን’ነው ግን?›› አለ ተገርሞ፤ ጥያቄ አልነበረም፡፡ አክቲቪስቱ ግን መልስ መስጠት ጀመረ…

‹‹ታሪኩ ረዥም ነው…››

እንግዳው፡- ‹‹የምኑ?››

አክቲቪስቱ በአግራሞት ዞር ብሎ እንግዳውን ተመለከተና ‹‹የተለያየንበት ነዋ?!›› አለው፡፡ እንግዳው ገባኝ ለማለት ጭንቅላቱን ከወዘወዘለት በኋላ ለማውራት የፈለገውን አክቲቪስት ዕድሉን፣ ለማድመጥ ተመቻቸለት…

‹‹ሁሉም ነገር የጀመረው የሕይወት ተፈራን ‘Tower In The Sky’ መጽሐፍ በገዛ እጄ ጨቅጭቄ ያስነበብኳት ጊዜ ነው፡፡ እሷ መጽሐፉን የተረዳችበት መንገድ እኔ ከተረዳሁበት በተቃራኒ መንገድ ነበር…›› አለ አክቲቪስቱ፡፡

‹‹እንዴት ተረዳችው?›› ጠየቀ እንግዳው፡፡

‹‹ሕይወት ተፈራ ከቤተሰቧ የተጣላችለት፣ ቦይፍሬንዷን ያጣችለት፣ የታሰረችለትና የተሰቃየችለት የለውጥ ምኞት የራሷን እንኳን ቤተሰብ ሳታፈራ አንድ የትዝታ መጽሐፍ ብቻ አሳቅፎ አስቀራት፡፡ ‹የአንተ እና የእኔም መጨረሻ ያው ነው› ባይ ናት፡፡››

‹‹ህም፣…›› አለ እንግዳው፡፡ ‹‹እውነት አላት!›› አክቲቪስቱ ዞር ብሎ ገላመጠውና መልሶ ወሬውን ቀጠለ፡፡

‹‹ከዚያ በኋላማ መቆጣጠር አቃተኝ፡፡ የሞቱ የ‹ያ ትውልድ› ታጋዮችን እየዘረዘረች… የሞቱት በከንቱ ነው፡፡ ‹ከነርሱ ይልቅ ዝም ብለው የራሳቸውን ኑሮ የኖሩ ሰዎች በግላቸው ስኬታማ ከመሆን አልፈው አገር የሚረከብ ቤተሰብ እያፈሩ ነው› እያለች መቆሚያ መቀመጫ አሳጣችኝ…››

‹‹እና እሷን ማሳመን አቃተኝ ነው የምትለኝ?...››

‹‹እንዳልኩህ እሷ ነገሩን የምትመለከትበት እና እኔ የምመለከትበት መንገድ የተለያየ ነበር፡፡፡… ችግሩ የመጣው አንድ ቀን ‹አክቲቪዝም› የሚባል ነገር አቁም፤ አለበለዚያ እንለያይ ስትለኝ ነው፡፡››

‹‹እንደዛ ከሆነማ እንዲያውም መለያየታችሁ ጥሩ ነዋ! ላትዛለቁ ምን አደከመህ?... እኔን የገረመኝ ግን አክቲቪስተነትህ እንዴት እሷን እንኳን ማሳመን ተሳነው? ሥራዬ ሰዎችን ማሳመን ነው ትል አልነበር እንዴ?››

‹‹ነገሩ ከማሳመን በላይ ነው፤›› አለ ሽርጡን እየፈታ፡፡

(ይቀጥላል)