Thursday, October 13, 2016

ፍቅረኛዬን ያያችሁ



የቀድሞ ፍቅረኛዬን - ሊሊን ካያችሁ - ውበት አይታችኋል። ሊሊን የጠበስኳት በገጣሚ ግሩም በለጠ ግጥሞች ነው። ግሩም አገር ያወቀው፣ ሊቅ ያደነቀው ገጣሚ አልነበረም። መጀመሪያ እኔ ብቻ ነበርኩ የማደንቀው። በኋላ ሊሊም ተጨመረችለት። የቀድሞ ፍቅረኛዬ ሊሊ ደግሞ ሙገሳ ስትወድ አይጣል ነው። ለነገሩ በኋላ ላይ ይበልጥ ሳውቃት ቁንጅናዋ ሙገሳ አይመጥነውም። እናም የመጀመሪያ ቀን የተዋወቅኳት የግጥምን በጃዝ ምሽት ላይ ነበር። ጎን ለጎን ተቀምጠን በጨዋታ ተግባባን። ዝግጅቱ አልቆ ስንወጣ ብሸኛት ትፈቅድ እንደሆን ጠየቅኳት እና ተስማማች። የግጥም ምሽት ላይ ስላገኘኋት በምትወደው ነገር ልቀላጠፋት ብዬ ስለግጥም ሳወራላት ቆየሁ።

“ግሩም በለጠን ታውቂዋለሽ?” አልኳት፤ አታውቀውም።

አንድ ግጥሙን በቃሌ ወጣሁላት፦

“በተውሶ ብርሃኗ፥  እንዳላደነቅኳት፣
ዓይንሽን አይቼ፥  ጨረቃዋን ናቅኳት።
በነጋ በጠባ፥ ደጁን እንዳልሳምኩኝ፣
ከንፈርሽን ቀምሼ፥ ሃይማኖቴን ተውኩኝ።
እንዲህ፣ እንዲህ እያልኩ፥ በተራ፣ በተራ፣
የቀድሞ ልማዴን፥ ሜዳ ላይ ስዘራ፣
ካንቺጋ መሆንን እንደስኬት ጣሪያ
ለጋ ከን‘ፈርሽን፣ ቀን ቀን ለመዋያ፣
እግርሽ መሐል ካለው፣ ማታ መቀበሪያ፣
ይሁነኝ እያልኩኝ፥ ሁሌ እባክናለሁ፣
በከንፈርሽ ስመሽ፣ ግደይኝ ብያለሁ፣
ውስጥሽ ለመቀበር፣ ሞትን እንቃለሁ…"

በጣም አሳቃት፤ “የግሩምን ግጥሞች የት አገኛቸዋለሁ?” አለችኝ።

ወቅቱን የጠበቀ ጥያቄ ስለነበር ደስ አለኝ። “ገበያ ውስጥ ያለ አይመስለኝም፤” አልኳት “እኔጋ ስላለ አውስሻለሁ።” የግሩምን ግጥሞች በቃሌ ስለማውቃቸው ብሰጣት የሚጎድልብኝ ነገር ያለ አይመስለኝም። ነገር ግን ሊሊን ደጋግሞ ለማግኘት፣ መጀመሪያ ለማዋስ፣ ቀጥሎ ለማስመለስ፣ ሠልሶ ቦርሳዋ ውስጥ ረስታው የሔደችውን መጽሐፍ ድጋሚ ለማስመጣት፣ በመጨረሻም አብሮ ተኝቶ ለመንቃት የነበረኝ አማራጭ ይኸው ብቻ ነው። ጀንጃኝ የምባል ዓይነት ወንድ አይደለሁም። ነገር ግን ዕድሉን ሳገኝ መጀመሪያ ቀልብ፣ ከዛ ሌላ ነገር የሚያቀልጥ ምላስ እንዳለኝ አውቃለሁ።

“በጣም ደስ ይለኛል” አለችኝ። ከሊሊ ጋር ስልክ መቀያየር በጣም ቀላል ነገር ሆነ። በማግስቱ ተገናኘን።