Sunday, September 25, 2011

ፍቅር፤ ከፍቅር እስከ መቃብር


ፍቅር የአየር ንብረት አይደለም፡፡ ሳይተነብዩት መጥቶ፥ ሳይተነብዩት ይሄዳል፡፡ የደምሴ እና የሰላም ፍቅርም እንዲሁ ሳይተነበይ መጥቶ ነው የሄደው:: ሲመጣ፥ ለሁለቱም መጣ፡፡ አካሔዱ ግን እንዳመጣጡ ቀላል አልነበረም፡፡

ደምሴ ቆፍጣና የፍልስፍና መምህር ነው፡፡ ሰላም ደግሞ ቀልቃላ ቢጤ የውበት ባለሙያ፡፡ ነገረ ሥራቸው ሁሉ እሱን ወንዳወንድ እሷን ሴታሴት ያደርጋቸዋል፡፡ የመጀመሪያ ሰሞን ‹‹በፊዚክስ ሕግ ተቃራኒዎች ይሳሳባባሉ›› ይላት ነበር ፍቅራቸውን ሲገልጸው፡፡ ኋላስ?!

ደምሴ እና ሰላም የተዋወቁት የሰው ሠርግ ላይ ነው፡፡ አጋጣሚ ጎን ለጎን አስቀመጣቸው፣ አጋጣሚ እሷን መኪና አሳጣት እና ወደፎቶ ፕሮግራም በእሱ መኪና ሄደች፡፡ ሁሉም በአጋጣሚ ፈጠነ፡፡ ደምሴ ሲያወሩት የሚያወራ፣ ሲዘጉት የሚዘጋ ዓይነት ሰው በመሆኑ ከሰላም ተጫዋችነት ጋር በጊዜው ሰምሮ ነበር፡፡

ሲመሽ ወደ ቤቷ ሸኛት፡፡ መኪና ውስጥ ትንሽ አወጉ፡፡ ‹‹በነገራችን ላይ ሰላም እባላለሁ›› አለችው፡፡

‹‹ኦው!›› አለ፤ ለካስ እስካሁን ስማቸውን አልተለዋወጡም፡፡

‹‹ደምሴ እባላለሁ፤›› አላት፡፡

‹‹ደምሴ?›› አለችው፡፡ ‹‹አዎ›› አላት፤ የገረማት ትመስላለች፡፡ ለምን እንደገረማት ግን እራሷም አልገባትም፡፡ ምናልባት ጨዋታው እንዲቀጥል ፈልጋ ይሆናል፡፡

‹‹ደምሴ ማለት ደምስሴ ማለት ነው፤›› የፍልስፍና ማብራሪያውን ሳያስበው ማዥጎድጎድ ሊጀምር ነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን ምኞቶቻቸውን በልጆቻቸው ማሳካት ይፈልጋሉ፡፡ ምናልባት የኔ ወላጆች አድጌ እንድደመስስላቸው የሚፈልጉት ጠላት ሳይኖራቸው አይቀርም ነበር፡፡ ያለዚያ ደምሴ አይሉኝም ነበር፡፡››