Thursday, November 28, 2013

የምን ሙስና?

‹‹እና ምን ላድርግ አጎቴ? አውቶቡሶቹ ከገቡ’ኮ ስድስት ወር አለፋቸው፡፡ መጋዘኑ ውስጥ ቆመው በከረሙ ቁጥር ዋጋቸው እየቀነሰ እንደሚሄድ ዘነጋኸው!››

የገንዘብ ሚኒስትሩ አጎቱ በዝምታ ተዋጡ፡፡

‹‹እስኪ ማታ እንገናኝና እንመካከርበት…››

***

በሳምንቱ ሼባ ሪዞርት የተባለ፣ ገና ግንባታው ያልተጠናቀቀ ሆቴል በአገሪቱ ውስጥ ካሉት አምስት የአውቶቡስ አስመጪዎች አራቱን የአውቶቡስ አስመጪዎች ለጨረታ የዋጋ ሰነድ እንዲያስገቡ ጠየቃቸው፡፡ ይህ በሆነ በሳምንቱ ሼባ ሪዞርት ‹‹የተሻለ አማራጭ በማግኘቱ›› ጨረታውን መሰረዙን ተናገረ፡፡ ሌላ አንድ ሳምንት አለፈ፡፡

የገንዘብ ሚንስቴር ሚኒስትር፣ የአስተዳደር ክፍል ኃላፊዎችን ሰብስበው በነባሮቹ የሠራተኞች ማመላለሻ አውቶቡሶችና፣ የሠራተኞችን ምቾት ስለመጠበቅ አዋሩዋቸው፡፡… አውቶቡሶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲገዙ የመወሰኑ ወሬ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመሰማቱ ሠራተኞች ተደሰቱ፡፡ ሚኒስትሩ በዚህ መሐል ለሙስና መንገድ እንዳይከፈት በአገሪቱ ካሉት አምስቱም የአውቶቡስ አስመጪዎች የዋጋ ማቅረቢያ በታሸገ ኤንቨሎፕ እንዲያቀርብ አስጠነቀቁ፡፡

***

ከአምስቱም አቅራቢዎች በዝቅተኛ ዋጋ አውቶቡስ ማቅረብ የቻለው ድርጅት አውቶቡሶች አስረክቦ ሒሳብ ተረከበ፡፡ ያኔ ሚኒስትሩ ስልክ ተደወለላቸው፤ ከወንድማቸው ልጅ!

‹‹ሃሎ…›› አሉ ሚኒስትሩ፡፡

‹‹አጎቴ… አመሰግናለሁ፡፡ በዕቅዳችን መሠረት ትርፉን ለሪዞርቱ ግንባታ ማስኬጃ እናውለዋለን፡፡ ቀሪውን ደግሞ ፈቃዱን ልቀይረውና የቢሮ ዕቃ ባስመጣበት ይሻላል…›› ሌላም፣ ሌላም… ‹‹… ለማንኛውም አንተ አስብበት››

አጎት ማሰባቸውን ቀጠሉ፡፡

Friday, October 18, 2013

ነጻ መሆንህ እስኪረጋገጥ ወንጀለኛ ነህ! (አጭር ልቦለድ)‹‹በእግዚአብሔር ስም እምልላችኋለሁ የማውቀው ነገር የለም…›› አለ እየጮኸ፡፡

‹‹ገልብጡት›› አለ ኮማንደሩ፤ አላመነውም ነበር፡፡

ከግራና ቀኙ ቆመው የነበሩት ሁለቱ ፖሊሶች ገፍትረው በአፍጢሙ ደፉት፡፡ ወለሉ የአፈር ስለነበር ብዙም አልተጎዳም፡፡ እግሮቹ ቋንጃ ላይ ወፈር ያለ ቧንቧ ብረት አስገብተው እግሮቹን የኋልዮሽ በመጎተት በጠፍር መሳይ ገመድ ከወገቡጋ አሰሯቸው፡፡ የቧንቧ ብረቱን ዳርና ዳር ይዘው ሲያነሱት ቁልቁል ተዘቀዘቀ፡፡ አንጠልጥለው ግድግዳው ላይ የተሰኩ ሁለት አግድም ምሰሶዎች ላይ ሰቀሉት፡፡

‹‹አሁንስ አትናገርም?›› አለው ኮማንደሩ፡፡

‹‹ኧረ እኔ ምንም የማውቀ…›› የጀመረውን ሳይጨርስ በፊት አንደኛው ፖሊስ በያዘው ደረቅ ጎማ ጀርባውን አደረቀው፡፡

‹‹እውነቱን ትናገራለህ ወይስ አትናገርም?›› አለው ኮማንደሩ በድጋሚ፤ ከመናገር ይልቅ ዝም ማለት ያዋጣል በማለት ዝም አለ፡፡

‹‹ትናገራለህ፣ አትናገርም›› አለው ኮማንደሩ፤ ዝም አለ!

ሁለቱም ፖሊሶች በደረቅ ጎማቸው ተፈራረቁበት፤ ‹‹እናገራለሁ፣ እናገራለሁ…›› አለ በጩኸት፡፡ ዱላውን አቆሙለት ነገር ግን የሚናገረው ስላልነበረው ዝም አለ፡፡

‹‹ተናገራ፣…›› አለ ኮማንደሩ በብስጭት ጩኸት እያምባረቀ ከጥቂት ደቂቃዎች ዝምታ በኋላ፡፡

‹‹እ…ግ…ዚ…አ…ብ…ሔ…ር…ን… ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡›› አለ የመሐላውን እያንዳንዷን ድምፅ አጥብቆ እየጠራ፡፡ ቁጥሩን ለማያስታውሰው ጊዜ ሁለቱ ፖሊሶች በደረቅ ጎማቸው ጀርባው ላይ ተረባረቡበት፡፡

‹‹አትናገርም፣… ›› አለ ኮማንደሩ፡፡

‹‹ምን ልናገር…? በእግዚአብሔር አታምኑም… ኧረ እባካችሁ…››

‹‹እስከ ጥዋት ድረስ አስብበት… እስክትናገር ድረስ ከዚህ አትወርድም›› ብሎት ኮማንደሩ ክፍሉን ለቆ ወጣ፡፡ ሁለቱ ፖሊሶች እጆቹን በካቴና ጠርንፈው ሲያበቁ ኮማንደሩን ተከትለው ከወጡ በኋላ በሩ በላዩ ላይ ተጠረቀመ፡፡ ቤቱ ዓይን በሚያወጣ ጨለማ ተዋጠ፡፡ እንደዘቀዘቁት ይቆያሉ ብሎ አላመነም ነበር፡፡ ከአሁን አሁን አንዳቸው ተመልሰው ይመጣሉ ብሎ አሰበ፣ ተመኘ፣ ፀለየ - ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡