Friday, March 16, 2012

እውነት እና እስር ቤት


“የኔ ውድ! እውን እናትሽን ገድሏል ያሉሽን አምነሽ ተቀበልሻቸው? አዎ! እናትሽን አልወዳቸውም ነበር፤ ግን እኮ እርሳቸውም አይወዱኝም ነበር!

“በእናትሽ ሞት ተጠርጥሬ እስርቤት ከገባሁ ወዲህ ስለእውነት ያለኝ አመለካከት ተቀይሯል፡፡ እውነት የለም! ያለውም ቢሆን ጥቅም የለውም፡፡ ቢኖረውማ እኔን እስር ቤት ሳይሆን የክብር ኒሻን ነበር የሚያሸልመኝ፡፡

የኔ ውድ! አንቺ የኔን ዲስኩር ለመስማት ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደማይኖርሽ አውቃለሁ፡፡ ግን አማራጭ የለኝም፡፡ ‹እወድሻለሁ፣ እወድሃለሁ› ተባብለን በፍቅር ከተለያየንበት ከዚያን ቀን ወዲህ ዓይኔን ማየት እንኳን እንዳስጠላሽ አውቃለሁ፤ አልፈርድብሽም፡፡ የናቷን ገዳይ ባልዋን ማየት የምትፈልግ ሴት የታለች?

“ይሄን ደብዳቤ ስጽፍ ተስፋ ያደረግኩት ‹እውነት ነፃ ያወጣኛል› ብዬ አይደለም፡፡ እውነት ነፃ እንደማያወጣኝ እዚሁ እስር ቤት ተምሬያለሁ፡፡ እውነቴ ልክ እንደነፃነቴ በሌሎች እጅ ወድቋል፡፡ ይልቅስ የኔ ውድ! እኔ ተስፋ ያደረግኩት በማህፀንሽ ያለው እውነት እንደሌላው ነገር ሁሉ ውሸት ሆኖ እንዳይቀር ነው፡፡

“ስለዚህ የኔ ውድ! የምጨቀጭቅሽ ስላሳለፍነው ጣፋጭ የፍቅር ዘመን፣ የቤተሰቦቻችንን ቅሬታ ችላ ብለን ስለከፈልነው መስዋዕትነት ወይም በትዳር ያሳለፍናቸው አምስት ዓመታት ተመልሰው ይመጣሉ የሚል ተስፋ ኖሮኝ አይደለም፡፡ እንደሱማ ቢሆን ሌላው ቀርቶ ጭቅጭቃችንም ይናፍቀኛል፡፡ የኔ ውድ! በእኛ እውነትና ውሸት የሁለት ወር ፅንስ ልጃችን ሁለተኛ ሟች እንዳይሆን የመጨረሻ ሙከራ ለማድረግ ነው የኔ ድካም፡፡
“ያቺን የተረገመች ቀን አልረሳትም፡፡ ትዝ ይልሻል የኔ ውድ! የዛን ዕለት ጠዋት ስንለያይ ‹ማታ የምስራች ይዤልሽ እመጣለሁ› ያልኩሽ? ታዲያ ምንስ ቢመረኝ፣ ምንስ ቢከፋኝ የእናትሽን ሞት ‹የምስራች› የምልሽ ይመስልሻል?

“የዛን ዕለት የሚኒስትሩን አለቃዬን ምስጢር የማጋልጥበት ቀን ነበር፡፡ ሚኒስትሩ አለቃዬ በሃብት ምዝገባ ወቅት ያስመዘገቡት መቶ ሺህ ብር የማይሞላ መሆኑን አውርተን የተሳሳቅንበት ምሽት ይረሳሻል ብዬ አላስብም፡፡ ያኔ ነበር እርሳቸውን መሰለል የጀመርኩት፡፡

“እንደገመትኩት ሰውዬው በሚስታቸው እህት በኩል የሚሊዮን ዶላር ሸቀጦችን ያለታክስ እያስገቡ የሚቸረችሩ የተዋጣላቸው ‹የመንግስት ሌባ› ናቸው፡፡ እርሳቸውን ከሚያክል ግንብ’ጋ በቀላሉ መላተም ስለማይቻል፣ ሸቀጦቻቸውን የሚያሳልፉበትን እያንዳንዷን መንገድ በቪዲዮ ለመቅረፅ ወሰንኩና በስንት ድካም ተሳካልኝ፡፡ ይህን ሳልነግርሽ መቀመጤ ‹አርፈህ ተቀመጥ› ትይኛለሽ ብዬ ፈርቼ አይደለም፤ ለደህንነትሽ አስቤ ነበር፡፡

“የዛኑ ዕለት የ‹አዲስ ፖለቲካ› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አግኝቼ የቪዲዮውን አንድ ቅጂ ሰጠሁት፤ ሌላኛውን ቅጂ መኝታችን ስር ሸሽጌው ነበር፡፡

“ለጋዜጣው አዘጋጅ የቪዲዮ ሲዲውን ሰጥቼው ስመለስ÷ እናትሽ ደወሉልኝ፡፡ ያለወትሯቸው በተለሳለሰ አንደበት በጥብቅ እንደሚፈልጉኝና ወደርሳቸው መምጣቴን ላንቺ ሳልናገር መሄድ እንዳለብኝ ነገሩኝ፡፡ ከአጠገባቸው ሰው እንዳለ ከንግግራቸው ቢያስታውቅም እኔ ምንም አልተጠራጠርኩም፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅሜ ፍቅር አወርዳለሁ በማለት ወደቤታቸው በረርኩ፡፡

“እዚያ ስደርስ ግን የጠበቀኝ ነገር የተለየ ነበር፡፡ እናትሽ በጥይት ተገድለው መሃል ሳሎን ውስጥ ተዘርረዋል፡፡ የተገደሉበት ሽጉጥ ራቅ ብሎ ወድቋል፡፡

“ደነገጥኩ፤ መጀመሪያ ላይ እናትሽ ራሳቸውን ያጠፉ መስሎኝ ነበር፡፡ ራሱን የሚያጠፋ ሰው ደረቱ ላይ አይተኩስም ብዬ አሰብኩ፡፡ ወንበዴ እንደገደላቸው አመንኩ፡፡

“ከቤቱ ውስጥ ምንም እቃ እንዳልተወሰደ ሲገባኝ ወንበዴው አሁንም ጊቢው ውስጥ ይኖራል በማለት ሽጉጡን አንስቼ ቀና ስል ‹እጅ ወደላይ!› የሚል ድምፅ ሰማሁ፡፡ ፖሊሶች ነበሩ፡፡

“ራሴን ነፃ ማውጣት በማልችልበት ሁኔታ እጅ ከፍንጅ ተይዤ እስር ቤት በገባሁ በሳምንቴ የ‹አዲስ ፖለቲካ› ጋዜጠኛውም የዛኑ ዕለት በ‹አሸባሪነት› ተጠርጥሮ መታሰሩን ሰማሁ፡፡ ቤቱ ተበርብሮ፣ ብዙ የቪዲዮና የጽሁፍ ማስረጃዎች እንደተገኙበትም ሰምቻለሁ፡፡ ይሄን ስሰማ ነበር የኔ እናትሽ ቤት ተጠርቶ መሄድ፣ የእናትሽ መገደል እና የጋዜጠኛው ‹አሸባሪ› መባል ድምር እውነታ እንዳላቸው መጠርጠር የጀመርኩት፡፡

“የኔ ውድ! የእውነት ዋጋ ሕይወት ነው፡፡ የኔን ተስፋም እስርቤት በልቶታል፡፡ ይህን የምነግርሽ ፍራሻችን ስር ያለውን ቪዲዮ አውጥተሸ ነፃ እንድታወጪኝ አይደለም፡፡ እሱ ቪዲዮ አጥፊያችን ስለሆነ ድራሹን አጥፊው፡፡ እኔ የምፈልገው አንቺ እና ልጃችን በሰላም እንድትኖሩ ነው፡፡

“ለዘላለም እወድሻለሁ፡፡”

በአንድ የተንጣለለ ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብለው ሚኒስትሩ ሲያነብ ይሰሙ የነበሩት ሦስት ሰዎች በድንጋጤ ፊታቸው ነጥቷል፡፡

“ይሄን ደብዳቤ እንዴት አገኛችሁት?” ሚኒስትሩ ጠየቁ፡፡

“ባለቤቱ ጠይቃው አታውቅም’ንጂ ምግብ በቤት ሠራተኛዋ ትልክለታለች፡፡ የምግብ ሳህኑ ውስጥ ከትቶት ነው ያገኘነው፡፡ ቁጥጥራችን ጥብቅ ነው፡፡”

በተመሳሳይ ሰዓት፤ የእስረኛው ባለቤት የእናቷ ሞት ዕለት ፍራሽ ሲያወርዱ ተገኘ ብላ ሠራተኛዋ የሰጠቻትን ሲዲ ከፍታ እየተመለከተች ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ እምብዛም ግልፅ ያልሆነላትን ቪዲዮ እየተመለከተች ስታስብ የነበረው ስለባሏ ነበር፡፡ እንኳን ሰው ዶሮ ደፍሮ የማይገድለው ባሏ፣ ያውም የገዛ እናቷን ገደለ ሲሏት ለማመን ተቸግራለች፡፡ ሆኖም ነገሩ እስኪጣራ ላታገኘው ወስናለች፡፡

ቪዲዮውን ተመልክታ ስትጨርስ አጥብቃ ያሰበችው በቪዲዮው ስለተመለከተችው ነገር ሳይሆን ባሏ ለምን ሲደብቃት እንደኖረ ነው፡፡ ባሏ ከጠበቀችው በላይ ምስጥራዊ እንደሆነ ይሰማት ጀምሯል፡፡ ‹እናቴን አልገደላት ይሆናል› ብላ ያዳፈነችው ጭላንጭል እምነት ሲከስም ተሰማት፡፡ ዓይኖቿ እምባ አቆረዘዙ፡፡

እምባ ባቆረዘዙት ዓይኖቿ በመስኮቱ አሻግራ ስትመለከት ፖሊሶች ወደግቢው ዘልቀው ወደበሩ ሲያመሩ ተመለከተች፡፡ ምን እንዳነሳሳት ባይታወቃትም ሲዲውን በመስኮቱ ወርውራ አትክልቱ ውስጥ ጣለችው፡፡ ፖሊሶቹ ገቡ፡፡

“አቤት! ችግር አለ?” ጠየቀች፡፡

“ባለቤትሽ በሌላ ወንጀል ተጠርጥሯል… ፍተሻ ለማድረግ ነው የመጣነው፤” አንደኛው ፖሊስ የማዘዣ ወረቀት ሰጣት፡፡

“ሌላ ወንጀል?” ጠየቀች - ማንም ምንም መልስ አልሰጣትም፡፡

ፖሊሶቹ ትኩረታቸው ሁሉ ፍራሹ እና በቤቱ ያሉ ቪዲዮ ሲዲዎች ላይ መሆኑን ስትመለከት ‹ሌላ ወንጀል› የተባለው ምን እንደሆነ ገባት፡፡ ‹በዚህ ዓይነት፤› አለች ለራሷ ‹የመጀመሪያው ወንጀልም እውነት ላይሆን ይችላል፡፡› በተስፋ ማሰብ ጀመረች፡፡

1 comment: