Sunday, September 25, 2011

ፍቅር፤ ከፍቅር እስከ መቃብር


ፍቅር የአየር ንብረት አይደለም፡፡ ሳይተነብዩት መጥቶ፥ ሳይተነብዩት ይሄዳል፡፡ የደምሴ እና የሰላም ፍቅርም እንዲሁ ሳይተነበይ መጥቶ ነው የሄደው:: ሲመጣ፥ ለሁለቱም መጣ፡፡ አካሔዱ ግን እንዳመጣጡ ቀላል አልነበረም፡፡

ደምሴ ቆፍጣና የፍልስፍና መምህር ነው፡፡ ሰላም ደግሞ ቀልቃላ ቢጤ የውበት ባለሙያ፡፡ ነገረ ሥራቸው ሁሉ እሱን ወንዳወንድ እሷን ሴታሴት ያደርጋቸዋል፡፡ የመጀመሪያ ሰሞን ‹‹በፊዚክስ ሕግ ተቃራኒዎች ይሳሳባባሉ›› ይላት ነበር ፍቅራቸውን ሲገልጸው፡፡ ኋላስ?!

ደምሴ እና ሰላም የተዋወቁት የሰው ሠርግ ላይ ነው፡፡ አጋጣሚ ጎን ለጎን አስቀመጣቸው፣ አጋጣሚ እሷን መኪና አሳጣት እና ወደፎቶ ፕሮግራም በእሱ መኪና ሄደች፡፡ ሁሉም በአጋጣሚ ፈጠነ፡፡ ደምሴ ሲያወሩት የሚያወራ፣ ሲዘጉት የሚዘጋ ዓይነት ሰው በመሆኑ ከሰላም ተጫዋችነት ጋር በጊዜው ሰምሮ ነበር፡፡

ሲመሽ ወደ ቤቷ ሸኛት፡፡ መኪና ውስጥ ትንሽ አወጉ፡፡ ‹‹በነገራችን ላይ ሰላም እባላለሁ›› አለችው፡፡

‹‹ኦው!›› አለ፤ ለካስ እስካሁን ስማቸውን አልተለዋወጡም፡፡

‹‹ደምሴ እባላለሁ፤›› አላት፡፡

‹‹ደምሴ?›› አለችው፡፡ ‹‹አዎ›› አላት፤ የገረማት ትመስላለች፡፡ ለምን እንደገረማት ግን እራሷም አልገባትም፡፡ ምናልባት ጨዋታው እንዲቀጥል ፈልጋ ይሆናል፡፡

‹‹ደምሴ ማለት ደምስሴ ማለት ነው፤›› የፍልስፍና ማብራሪያውን ሳያስበው ማዥጎድጎድ ሊጀምር ነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን ምኞቶቻቸውን በልጆቻቸው ማሳካት ይፈልጋሉ፡፡ ምናልባት የኔ ወላጆች አድጌ እንድደመስስላቸው የሚፈልጉት ጠላት ሳይኖራቸው አይቀርም ነበር፡፡ ያለዚያ ደምሴ አይሉኝም ነበር፡፡››

ሰላም ፈገግ አለች፡፡

‹‹እውነቴን ነው የምልሽ፤ በኢትዮጵያውያን ባሕል የልጅ ድርሻ ዘርን መተካት ብቻ አይደለም፡፡ እልህ መወጫ፣ መበቀያ ወይም ሕይወትን መቀየሪያ ነው፡፡ ወንድ ልጅ ሲሆን ደግሞ ጫናው ይበዛል፡፡ ደብድቦም፣ ገድሎም ቤቱን የሚያስከብር እንዲሆን ከስሙ ጀምሮ እስከአስተዳደጉ ጥረት አይለየውም፡፡››

‹‹እሺ እኔስ ለምን ሰላም ተባልኩ?›› አለችው፡፡

አሰብ አደረገና ‹‹ምናልባት እናትና አባትሽ በልጅ እጦት እየተጣሉ ከነበረ ሰላም የወረደላቸው ባንቺ ይሆናል….›› ግምቱን ሰነዘረ፤ ግምቱ ትክክል ስለነበር ከትከት ብላ ሳቀች፡፡

ሲተዋወቁ የመጀመሪያ ቀናቸው አይመስልም፡፡ በጣም ቅልል የሚል ሰው ሆነላት፡፡ ስልክ ተለዋወጡ፡፡ ከመኪናው ስትወርድ ከንፈሩን ስማው እንደወረደች እንኳን አልታወቃትም ነበር፡፡

ሁሉም ነገር የሆነው በጣም በፍጥነት እና በጣም ደስ በሚል ሁኔታ በመሆኑ ሳይጠያየቁ በጀመሩት ፍቅር ልባቸው ጦዟል፡፡ ለወትሮው ‹‹ፍቅርና ገንዘብ እንደመንዛሪው ነው›› እያለ የሚተርተው ደምሴ የሰላምን ፍቅር ያልቅብሻል ብሎ ሳይሰስት በየቀኑ ይመነዝረው ጀመር፡፡ እሷም ሁለመናዋን ሳትሰስት እንደሰጠችሁ ሁሉ!

አንድ ቀን፥ ፍቅር ሰርተው ሲጨርሱ፤ ‹‹ታውቂያለሽ?›› አላት፡፡ ‹‹ታውቂያለሽ፤ የፍቅር ግንኙነት የፍቅርን ጣዕም ያጠፋዋል ብዬ አምን ነበር፡፡ አሁን ግን ሲገባኝ፤ የፍቅር ጣዕሙ የሚያልቀው፥ ከትክክለኛዋ ሴት ጋር ካልሆነ ነው፤›› ብሏት መልሷን እንኳን ሳይጠብቅ ‹በአፉ መሳም› ይስማት ቀጠል፡፡

የደምሴና ሰላም ሦስት ወራት በፍቅር አለፉ፡፡ ወሬያቸው፣ ምግባራቸው እና ምኞታቸው ሁሉ ፍቅር ነበር፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ ግን የደምሴ ፍልስፍና እውነት እየሆነ የመጣ መሰለ፡፡ ፍቅራቸው ተመንዝሮ ወደማለቁ ተጠጋ፡፡

ፍቅር ሰርተው ሲጨርሱ፥ በጋራ ሻወር ይወስዳሉ፡፡ ከዚያም፣ እንደተለመደው ሰላም ገላዋን በሎሽን፣ ከንፈሯን በቀለም፣ ዓይኗን በኩል ስታሰማምር ቁጭ ብሎ ይመለከታታል፡፡ በፊት፣ በፊት ውበቷን በማድነቅ ስሜት ነበር የሚያያት አሁን፣ አሁን ግን ‹መቼ ትጨርስ ይሆን?› እያለ ነው፡፡ አልፎ፣ አልፎ ‹‹ዝም ብዬ ሳይሽ እኮ - ተኳኩለሽ ስትጨርሺ እግዜር የሰራት ሰላም ቀርታ ሌላ ሰላም የተፈጠረች ይመስለኛ›› ይላት ጀምሯል፡፡

‹‹ምን?.... በሜካፕ ብዛት ነው የምታምሪው ልትለኝ ነው?››

‹‹አልወጣኝም›› ይላታል፡፡

እየቆዩ፣ እየቆዩ ከፍቅራቸው ይልቅ ንትርካቸው በዛ፡፡ መንስኤው እሱ ‹‹እሷ ማንነቴን ልትለውጥ መፈለጓ ነው›› ብሎ ሲያስብ፤ እሷ ደግሞ ‹‹እሱ የማይለወጥ ሰው ስለሆነ ነው›› ትላለች፡፡

ሌላው ቀርቶ የጎፈረው ጺሙ ያጣላቸዋል፡፡ ይጣላሉ፣ ይታረቃሉ፡፡ ሲጣሉ ይነፋፈቃሉ፣ ሲታረቁ ለአንድ ሳምንት ይጣጣማሉ፣ መልሰው ይጣላሉ፡፡ ይሄ ዑደት ሲደጋገም ሰላምን አሰለቻት፡፡ ሰላም ከዚህ ሰንሰለታዊ ሕይወት መውጣት የምትችለው ሌላ ወንድ በማግኘት እንደሆነ አሰበች - በሐሳቧ ተጓዘች፡፡

ደምሴና ሰላም እንደተለመደው በትንሽ ንትርክ ተከራክረው በተለያዩ ሳምንታቸው ገደማ ሰላም ከአንድ ሰው ጋር መቀጣጠር ጀመረች፡፡ መቀጣጠር በጀመረች በጥቂት ቀናት ውስጥ ደምሴ እንደገና ደወለ፤ ኩርፊያው አልፎለታል ማለት ነው፡፡ ግን ረፍዷል፡፡ የሰላም ልብ ላዲሱ ሰውዬ መቅለጥ ጀምሯል፡፡ በዚያ ላይ ከደምሴ እስር የምትላቀቀው በዚህ ውስጥ እንደሆነ ተሰምቷታል፡፡

ችግሩ ለደምሴ ይሄንን ለመንገር ድፍረቱ ከየት ይምጣ የሚለው ነው፡፡ እንዳኮረፈ ሰው አናግራው ስልኩን ዘጋችበት፤ በማግስቱ ደግሞ ደወለ ሳታነሳው ቀረች፡፡ ደጋግሞ ደወለ፥ በሐሳቧ ቁርጡን ልትነግረው ወስና ቀጠረችው ሲገናኙ ግን ይህንን ማድረግ አቅሙ አልነበራትም፡፡ እንዲያውም ወደቤቷ ሸኝቷት ከመኪናው ልትወርድ ስትል ሲስማት መልሳ ስማዋለች፡፡

ሕይወቷ ሐዲዱን ሳተ፡፡ አዲሱ ሰው ጠዋት የሳማት እንደሁ ደምሴ ማታ ይስማታል፡፡ አፍቃሪዋ ሰላም አስመሳይ ተዋናይት ሆነች፡፡ ከዚያኛው ጋር ሁና የደምሴን፣ ከደምሴ ጋር ሁና የዚያኛውን ሰው ስልክ እንዳመሉ ማስተናገዱን ተጠበበችበት፡፡ ጊዜው ነጎደ፡፡ ሰላም ለውጥ ፈላጊ አፍቃሪ መሆኗ ቀርቶ ጥፋቷን ለመሸፈን ስትል፣ ወይም መውጫው መንገድ ጠፍቷት የምትንከራተት ‹‹እንዳሻችሁ ጋልቡኝ›› ባይ ሴት ሆና አረፈችው፡፡

ሰላም በጊዜ ሒደት ውስጥ ሁለቱንም ወንዶች የምትወዳቸው ሁነው አገኘቻቸው፡፡ ሁለቱንም ማጣት ቀላል ሊሆንላት አልቻለም፡፡ ሁለቱንም አብሮ ማስኬድም የድብብቆሽ ስቃይ አለው፡፡ በሁለት አጣብቂኝ ውስጥ ሁና መፍትሄ እስኪመጣላት የያዘችው፥ ‹‹በሁለት እግር ሁለት ዛፍ የመውጣት›› ሙከራዋ አላዛለቃትም፡፡ ሁለቱም ወንዶች ነቅተውባት የሆዳቸውን በሆዳቸው አብተዋል፡፡

ውድ አንባቢያን፡-
የዚህ ታሪክ መጨረሻ ሁለት አማራጮች አሉት፡፡ አንዱን መምረጥ የእናንተ ድርሻ ነው፡፡

አማራጭ አንድ
አዲሱ የሰላም ፍቅረኛ ዛሬ አብሯት ሊያድር እንደሚፈልግ ነግሯታል፡፡ እሱ ትንሽ የሚያቆየው ሥራ ስላለው፥ ከከተማው አንድ ዳርቻ የሚገኝ ፔንሲዮን ጠቁሟት እዚያ ክፍል በጊዜ እንድትይዝና እንድትጠብቀው ነግሯታል፡፡

ይህንን ያደረገው ሆነ ብሎ ነው፡፡ የፔንሲዮኑ አከራዮች የሷን አድራሻ ብቻ ነው የሚይዙት፥ እሱ ሹልክ ብሎ ይገባና ገድሏት እንዳገባቡ ይወጣል - ዕቅዱ ይኸው ነው፡፡

ደምሴ በበኩሉ በዚሁ ቀን ደውሎ እንዲገናኙ ሲጠይቃት፥ ሰላም ‹‹አይመቸኝም›› በማለቷ ለብዙ ጊዜ የተዘጋጀበትን ድግስ ደግሶላታል፡፡ ከቢሮዋ ስትወጣ ጀምሮ በተከራየው መኪና ይከታተላት ጀመር፡፡ የገባችበትን ፔንሲዮን አየ፤ ሰውየው አብሯት አልመጣም፡፡ እዚያው አካባቢ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ሰውየውን እየተገላመጠ ሲገባ አየው፡፡ ቀድሞ ባጠናው አጥር ተንጠልጥሎ ገብቶ ተከተለው፡፡ በኮሊደሩ ተከልሎ ሰውየው የሚገባበትን ክፍል አስተዋለ፡፡ ሰውየው ሲገባ፥ ደምሴ በዝግታ ወደክፍሉ አመራ፡፡ በሩ ላይ ጆሮውን ለጥፎ አደመጠ፡፡ የመሳሳም የሚመስል ድምጽ ተሰማው፡፡ ደጋግሞ አዳመጠ፡፡ ብስጭቱ በረታ፣ ደሙ ፈላ፡፡ የሷ ድምጽ በከፊል ይሰማ ጀመር፤ ከምኔው ጀመሩ? የቅናት ስሜቱን መግራት አልቻለም፡፡ ራሱን ለመግዛት እና እርምጃ ለመውሰድ ደቂቃዎች ፈጀበት፡፡ በሩን በርግዶት ገባ፡፡ ሰውየው በድንጋጤ ፊቱን ወደደምሴ አዞረ፡፡

ደምሴ በሚመለከተው ነገር ግራ ተጋብቷል፡፡ ሰውየው በትራስ አፍኖ ሰላምን ጨርሷታል፡፡ ምን እየተካሔደ እንደሆነ ለማሰብ ጊዜ የለውም፡፡ ያቀባበለውን ሽጉጥ በሰውየው ደረት ላይ አነጣጥሮ ቃታውን ሳበ፡፡

አማራጭ ሁለት
አዲሱ የሰላም ፍቅረኛ ዛሬ አብሯት ሊያድር እንደሚፈልግ ነግሯታል፡፡ ሆኖም ሊዘገይ ስለሚችል እስከዛሬ የሚገናኙበት ሆቴል ውስጥ ክፍል ይዛ እንድትጠብቀው ነግሯታል፡፡

ሰላም አንዱ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብላ ፍቅረኛዋን እየጠበቀችው ነው፡፡ ደምሴ እንዳይደውልባት ስልኳን አጥፍታዋለች፡፡ በሩ ተንኳኳ፡፡ ከፊል ራቁቷን ነች፡፡ ፍቅረኛዋ ሰዐት አክባሪ ነው፡፡ ልክ በነገራት ሰዓት ከች በማለቱ ተደስታ በሙሉ ፈገግታ በሩን ከፈተችለት፡፡

አዲሱ ፍቅረኛዋ ብቻውን አልነበረም፤ ደምሴ አብሮት አለ፡፡ ከፊት ለፊቷ የምታየው ነገር ሰውነቷን አራደው፡፡ ከፊል እርቃኗን እንዳያዩባት ለመደበቅም የፈለገች መሰለች፡፡ ከንፈሯ ተንቀጠቀጠ እንጂ መናገር አልቻለችም፡፡ እንግዶቿ ያለግብዣዋ ገብተው በሩን ዘጉት፡፡ ምክንያቷን ሳያዳምጡ፣ ለስሜቷም ሆነ ለምላሽዋ ሳይጨነቁ ሰማይ በሚበሳ ድምጽ እየተፈራረቁ አምባረቁባትና ሲበቃቸው ወጡ፡፡

ሁለቱንም ማጣት ያልፈለገችው ሰላም ከሁለት አንዱንም ከማጣት የበለጠ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማት፡፡

ወድ አንባብያን፡-
ምርጫችሁ የቱ ነው? የቱንም ብትመርጡ የምርጫችሁ ቅጣት ግዞተኛ መሆናችሁ እንደማይቀር ጸሃፊው ያስባል፤ ምርጫችሁ ያውጣችሁ!!!

1 comment:

  1. ሁለተኛውን መርጫለሁ ምክንያቱም ሰላም እንድትሞት ስለማልፈልግ !!!

    ReplyDelete