Monday, December 6, 2010

የመንግስት ሠራተኛው የፍቅር ቀጠሮ (የdating እንጉርጉሮ)


ዕለቱ ሕዳር 27 ነው፤ የደሞዝ ቀን፡፡ ኪሱ በመቶ ብሮች ታጭቋል፡፡ ማታ የራት ግብዣ አለበት፡፡ የራት ግብዣው አቅራቢ እሱ ነው፤ ተጋባዧ ሜላት፡፡ ለዚህ የራት ግብዣ ብዙ ተዘጋጅቷል፣ በጣም ጓጉቷል፣ እንቅልፍ አጥቷል - በአራት ነጥብ ጉዳዩን ለማሳጠር ያክል የማይሆነውን ሆኗል፡፡

ሜላትን የተዋወቃት በፌስቡክ ነው፡፡ የጓደኞቹ ጓደኛ ፎቶ ላይ ‘Tag’ ተደርጋ አያት፡፡ ሒደቱ ቀላል ነበር፡፡ በመጀመሪያ ፎቶዋን ወደደው፡፡ ከዚያ ‘ፕሮፋይሏን’ ጎበኘ እና ወደደላት፤ በተለይ ‘Single’ መሆኗ ተመቸው፡፡ ለፌስቡክ ጓደኝነት ጠየቃት ተቀበለችው፡፡ ፎቶዎቿን በሙሉ አየ - በቀኝም፣ በግራም፣ በፊትለፊትም፣ በኋላም የተነሳቻቸው ፎቶዎቿ ያምራሉ፡፡ ለፌስቡክ ተራ ጓደኝነት ያንስባታል ብሎ አስቦ ለሌላ ነገር አጫት፡፡ ያንን ሌላ ነገር ሳይነግራት ‘Chat’ ላይ እየጠበቀ ስትገባ ያዋራት ጀመር፡፡ ለነገሩ እሷም ‘easy going’ መሆኗ ተመችቶታል፤ አስፈርቶታልም፡፡ ‘easy going’ መሆኗ ለእሱ ብቻ ካልሆነስ? ደግሞም አይሆንም፡፡

እሱ የመንግስት ሰራተኛ ነው፡፡ 1,600 ብር ተከፋይ የወር ደሞዝተኛ፡፡ ለነገሩ ከዚህችው ላይ ታክስ፣ የጡረታ አበል ምናምን ሲቆራረጥ ከ1,400 ብር በላይ ጥቂት አሥር ብሮች ናቸው የሚተርፉት፡፡ ታክስ የሚባል ነገር ያበሳጨዋል፡፡ “ይቺም ገቢ ሁና በገቢ ታክስ እና በቫት ተቀነጣጥባ ታልቃለች” እያለ ያማርራል፡፡ ምናልባት ብዙ ከተወራለት የጥር ወር ደሞዝ ጭማሪ በኋላ ተስፋ ሰንቋል - በደሞዙ ማነስ ላይማረር፡፡ ስንት ቢጨመርለት እንደማይማረር ግን አስልቶ አያውቅም፣ ማስላትም አይፈልግም፡፡

ዘወትር ማለዳ ቢሮው እንደገባ መጀመሪያ የሚከፍተው የፌስቡክ ገፁን ነው፡፡ “መንግስት በደሞዝ የበደለንን ያክል እኛም የሥራ ጊዜያችንን በፌስቡክ እያባከንን እንበድለዋለን” እያለ ይዝታል፡፡ ከወዳጅ ጓደኞቹ ጋር በስልክ “እንዴት ነህ፣ እንዴት ነሽ?” መባባል ሒሳቡ የትዬለሌ ነው፡፡ ካፍቴሪያ ተገናኝቶ መጨዋወትም ቢሆን መጨረሻ ላይ ሒሳብ መክፈል የሚባል ክፉ ነገር ስላለ አይሆንም፡፡ ፌስቡክ መፍትሄ ነው፡፡ የኢንተርኔት ግንኙቱም ሆነ የሥራ ሰዓቱ ብክነት በመንግስት በጀት ነው፡፡ ደሞዝ የማይሸፍነውን ቀዳዳ ፌስቡክ ይሸፍነዋል ብሎ ያምናል - የመንግስት ሠራተኛው፡፡ ጮክ ብሎ የማያማውን መንግስት በድብቅ ያጠቃው ይመስል ይህን እና መሰል አጋጣሚዎችን ይጠቀማል፡፡

ሜላት ሞልቃቃ ቢጤ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ስትስቅ ‘lol’ እያለች ነው፣ ስታወራ ‘wt r u doin’?’ እንጂ እንደሱ ‘What are you doing now?’ እያለች ነገር አታንዛዛም፡፡ የእሷን ምህፃረ ቃላት ለመፍታት ብዙ ጊዜ Googleን አስቸግሯል፡፡ አስቸግሮም፣ ተቸግሮም አልቀረ - ከብዙ ውትወታ በኋላ “እሺ እንገናኝ” አለችው፡፡ ስልክ ተለዋወጡ፣ ተደዋወሉ እና ተቀጣጠሩ፡፡ የሚገናኙበትን ቦታ የመረጠችው እሷ ነበረች፡፡ ብሉ ቶፕስ፡፡

እሱ የብሉ ቶፕስን ሰማያዊ ጣሪያዎች እንጂ ውስጡን አያውቀውም፡ ስለብሉ ቶብስ ያለው ግንዛቤ በበሩ ሲያልፍ ካየው ነገር አይበልጥም፡፡ ብዙ የውጭ ዜጎችና፣ የውጭ ቋንቋ የሚያዘወትሩ ሐበሾች የሚገቡበት ቤት ነው፡፡ ብሉ ቶፕስን በሜላት ሰበብ ሊያይ ነው - ደስ አላለውም፡፡ ብሉ ቶፕስ ውስጥ ጎራዴ ታጥቀው ገንዘቡን ሊያስተፉት የተዘጋጁ አስተናጋጆች እንደሚኖሩ ገምቷል፤ ፈርቷል፡፡

ከወር ደሞዙ አስተርፎ ልብስ ስለመግዛት አስቦ አያውቅም፡፡ የሚለብሳቸው ልብሶች ሁሉ ከተገዙ ሁለት ዓመት አልፏቸዋል፡፡ እስከዛሬ የወር ደሞዙን ለሻይ፣ ለምሳ እና ለትራንስፖርት ማብቃቃት ላይ እንጂ አለባበሱን ለማሳመሪያነት አስቦት አያውቅም ነበር፤ ዛሬ ግን አሰኘው፡፡

መስታወት ፊት ቆሞ ራሱን ገመገመ፡፡ መልከመልካም ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰጠው ሁሉም ነገር ያምራል፡፡ አለባበሱ ግን . . . ያስጠላል፡፡ ሊቀይረው የሚችለው የተሻለ ልብስ እንዳለ በአእምሮው ቆጠረ፡፡ የባሰ እንጂ የተሻለ የለውም፡፡ እዛች ሞልቃቃ ሜላት ፊት ደግሞ እንዲህ ሆኖ መቅረብ አይታሰብም፡፡ ወዲያውኑ ልብስ ለመግዛት አሰበ፡፡ ለሜላትም፣ ለብሉ ቶፕስም የሚመጥን ልብስ ሊገዛ ገበያ ወጣ፡፡ ከፒያሳ ጎዳና ዳርቻ ወደሚገኙት ቡቲኮች ነጎደ፡፡

ከአንድ ሰዓት በኋላ
አንዱ ቡቲክ ውስጥ አንድ ጅንስ ሱሪ በእጁ አንጠልጥሎ እንደያዘ፣ ግንባሩ ላይ በፊት ያልነበረ የደም ስር ተገትሮ ቆሟል፡፡ እሱም ቆሟል፣ ልቡም ቆሟል፣ አብዛኛው ነገር ቆሟል፡፡

“አንድ ሱሪ አራት መቶ ብር?” አለ ቆንጆዋ አሻሻጭ እንዳትሰማው ድመፁን ዝግ አድርጎ፡፡ እንደፍላጎቱ ቢሆን ይህቺ ቆንጆ የጠራችውን ሒሳብ ከፍሎ ቢወጣ ደስታውን አይችለውም ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው? አቅሙ አይፈቅድም፡፡ ተስፋ ሳይቆርጥ አንድ አሻንጉሊት የለበሳትን ሸሚዝ እያሳያት “ይሄስ ስንት ነው?” አላት፡፡ “ሁለት ከሰማንያ” አለችው ቆንጆዋ ልጅ አፏን ሞልታ፣ በፈገግታ፡፡ “ጥርስሽ ይርገፍ” አላላትም፡፡ በአንድ ሱሪ እና ሸሚዝ ግማሽ ደሞዙን ብትጠይቀውም፣ እሷም ከሱ የባሰች መሆኗን ያውቀዋል፡፡ እነዚያን ብልጭልጭ ልብሶች በሽያጭ እንጂ በግዢ አታውቃቸውም፤ አትደፍራቸውም፡፡

ዓይኖቹ ቡቲኩ ውስጥ በተሰቀሉት ልብሶች ላይ ተራወጡ፡፡ ቲ-ሸርቶች፣ የውስጥ ሱሪዎች፣ ካልሲ፣ ጫማ…. የቱን ገዝቶ የቱን ይተዋል? ደሞዙን ለቡቲኩ አስረክቦ ሲሄድ ታየው፡፡ የለበሰው ልብስ፣ ቡቲኩ ውስጥ የተሰቀሉት ልብሶች፣ ቆንጆዋ ሻጭ፣ ሞልቃቃዋ ሜላት፣ ብሉ ቶፕስ….. ሁሉም በአንድነት በምናቡ ተደቅነው ወጥረው ያዙት፡፡

ልብሱን ቢገዛስ ብሉ ቶፕስ የሚገባው ምን ይዞ ነው? ብሉ ቶፕስ ቢገባስ ወሩን የሚዘልቀው በምኑ ነው? “እኔ አምልሽ?” አላት፤ “እ…?” አለችው፡፡ “እዚህ አገር ልብስ የሚገዙት ሚሊዬነሮች ብቻ ናቸው እንዴ?” አላት፡፡ ፈገግ አለች፤ ፈገግ አላለም፡፡

አማራጮቹን አሰበ፡፡ አንድ የመንግስት ሠራተኛ ኪሱን እያሰበ የሚያመጣቸው አማራጮች ሁሉ ታዩት፡፡ የዛሬ ወጪ፣ የወር ገቢ፣ የወር ወጪ ታሰቡት፡፡ የሚመቻመች ነገር የለም፡፡ በመጡለት አማራጭ መፍትሄዎች ላይ ተመርኩዞ ወሰነ፡፡ ውሳኔው ቀላል ነው፤ ብዙ ወጪ የማይጠይቅ! ስልኩን ማጥፋት፣ ሜሮንን መቅጣት - ከዚያ በፌስቡክ አንድ መለኛ ውሸት ማስፈር፡፡ ፌስቡክ ያመጣውን ችግር ራሱ ፌስቡክ ይወጣው - አለቀ፡፡ 
----- ይቀጥላል ----

No comments:

Post a Comment