Tuesday, April 19, 2011

የመንግስት ሠራተኛው የፍቅር ቀጠሮ (Version: ከደሞዝ ጭማሪ በኋላ)



የመንግስት ሠራተኛው ከሜላት ጋር ላለመገናኘት የፈለገው የዛን ዕለት እንጂ ከጥር ወር የደሞዝ ጭማሪ በኋላ አይደለም፡፡ ስለዚህ ስልኩን ስላጠፋበትና ቀጠሮው ላይ ላልተገኘበት አሳማኝ ምክንያት እያሰሰ ነው፡፡ “እንዳስፈላጊነቱ አንዱን መግደል ነው” ሐሳቡ ፈገግ አሰኘው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ትምህርት ቤት እና መሥሪያ ቤት ሲቀር የገደላቸው ዘመድ አዝማዶቹ የመቃብር ቦታ ሳያጣብቡ አይቀሩም፡፡ “እስኪ ማን ሞተ ልበላት?” ብሎ አሰበ፡፡

ሦስት ቀናትን ያለፌስቡክ አሳለፈ፤ አቤት እንዴት ይከብዳል? ሜላትም አልደወለችም፤ ምናልባት በቀጠሮው ሰዓት ስልኩን አጥፍቶ ስለቀረባት አኩርፋው ይሆን? በስንት መከራ እሺ ያስባላትን ቀጠሮ “ድጋሚ እንዴት ነው የሚሆነው?” በመጨረሻ ሁነኛ መላ መጣለት፤ መቼም እናትን ከመግደል ማሳመም ሳይሻል አይቀርም፡፡

የፌስቡክ ግድግዳው ላይ እንዲህ ብሎ ጻፈ፡፡ “የእናቴ ድንገተኛ ሕመም አስደንግጦአችሁ፣ ከአጠገቤ ሳትለዩ የከረማችሁ ጓደኞቼ ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ፤ እናቴ አሁን በሙሉ ጤንነት ውስጥ ትገኛለች፡፡” ጓደኞቹ ባልሰሙት አስደንጋጭ ዜና ኮሜንታቸውን አዥጎደጎዱት፤ ለብዙዎቹ በmessage box ማስተካከያ ለመላክ ቢገደድም “ይሁና፤ ሜላትን መልሶ ለማግኘት ሲባል” እያለ ራሱን እያፅናና ነበር፡፡ በመጨረሻ ሜላት “I’m sorry” የሚል comment አሰፈረች፡፡ “ምን ማለቷ ነው? የኔ እናት መታመም አያሳስባትም ማለት ነው? ይቅርታ አታደርግልኝም ማለት ነው?” አዘነባት፡፡

ሜላት በመልዕክት ሳጥኑ ተጨማሪ መልዕክት ላከችለት፡፡ መልዕክቱ እፎይ የሚያስብል ነበር፡፡ “በእናትህ መታመም አዝኛለሁ፤ ደግነቱ አሁን ተሽሏቸዋል መሰለኝ፡፡ anyways, የዛን ዕለት ብሉ ቶፕስ ያልመጣሁት ካቅሜ በላይ የሆነ ችግር ገጥሞኝ ነው፡፡ ስደውልልህ ስልክህ switched off ይላል፡፡ ሰሞኑን የጠፋኸው አኩርፈኸኝ መስሎኝ ነበር፡፡ እንዳልተቀየምከኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ሌላ ጊዜ እንገናኛለን፡፡” መልዕክቱን አንብቦ ሲጨርስ “እናቴን ለሕመም ዳርጌት ሳበቃ፣ አልመጣሁም ነበር ትለኛለች እንዴ? እስካሁን የት ነበረች?” አለ ለራሱ፡፡ ደስ ብሎታል፤ በመቅረቷም ተናዶባታል - ጓጉቶ ሲጠብቃ ቀርታ ቢሆን ኖሮስ!?

ጊዜው እንደአመጣጡ እየነጎደ ሲጠበቅ የኖረው ጥር ወር ደረሰ፡፡ የደሞዝ ጭማሪው፣ እንደምንም ደሞዙን ሁለት ሺህ ብር አፋፍ ላይ አደረሰው፡፡ ግን ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ መንግስት የዋጋ ማረጋጊያ ብሎ የሸቀጦች ተመን ጣሪያን ቢደነግግም፣ ለሱ ግን እግዜር የሰጠውን ውበት አጉልቶ የሚያሳዩ ልብሶችን ዋጋ ዘንግቶታል፡፡ የዋጋ ተመኑ ነገር ለሱ ግራ ነው፤ እሱ የማይጠጣው ቢራና የማይቆርጠው ጮማ ዋጋ ቀንሶ፣ እሱ የሚያዘወትረው ሽሮ ግን ጨመረ፡፡ “ወዮ” ብቻ ነበር መልሱ፡፡

ሜላት ኑሮ መወደዱን የሰማች አትመስልም፤ ሳቅና ጫወታ ብቻ ያምራታል፡፡ “እሷ በደህና ጊዜ ካለው ተወልዳ ነው” እያለ ሲያስብ የገዛ ሁኔታው ግራ ያጋባዋል፡፡ “እኔስ እሷ ላይ ምን አጣበቀኝ? ካለው መጠጋቴ ይሆን?” ይላል፡፡ ካለው መጠጋቱ እንኳን አልነበረም፡፡ በግል ጥረቱ ሊያየው ያልቻለውን ምቾት ከሌሎች ፊት ላይ መመልከት ነው አምሮቱ - ከውስጥ፡፡

የመንግስት ሠራተኛው ካሁን አሁን ገቢዬን ከወጪዬ አመጣጥኜ የተረፈኝ እንደሁ ሜላትን እጋብዛታለሁ እያለ ቢታትርም እስካሁን አልተሳካለትም፡፡ ሰበብ አስባብ እየፈጠረ ቀጠሮ ሲያራዝም፣ ሲያራዝም ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡  “ይቺን የመሰለች ሲሳይ ገፍቼ፣ ገፍቼ እግዜር እራሱ አይምረኝም” እያለ ያስባል፡፡

በዚህ ሁሉ የፍቅር እና የችግር እሰጥ አገባ መሃል ‘የአባይ መገደብ’ የተሰኘ ታሪካዊ ኩነት ተወለደ፡፡ ዜናው ለሱም ሆነ ለማንኛውም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ አስደሳች ነበር፡፡ “ምን ዋጋ አለው?” ይላል እየቆዘመ “ቦንድ የሚባል ቦንብ ተከትሎት መጣ፡፡” ማታ፣ ማታ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተለያዩ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የወር ደሞዛቸውን በፈቃደኝነት ከመለገሳቸውም ባሻገር ቦንድ እየገዙ እንደሆነ ይናገር ጀመር፡፡ ጉዳዩ የሱን መሥሪያ ቤትም አንኳኳ፡፡

የመንግስት ሠራተኛው የዚህን ጊዜ ምርር ብሎ እንዲህ አለ “እኔ እንኳን አባይን ገድቤ 63 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ላጠራቅም፣ የምወዳትን ልጅ - ሜላትን አንድ ሊትር የማዕድን ውሃ መጋበዝ ያቃተኝ ሰው ነኝ፡፡” ይህንን ያለው ግን ለራሱ ነበርና የመንግስት ጆሮ አልደረሰም፡፡ ከደሞዙ ላይ መቶ ምናምን ብር ይቆረጥ ጀመር - ለአንድ ዓመት ያህል ይቆያል፡፡

ሜላትን ከዛሬ ነገ እጋብዛታለሁ፣ በዚያው አጋጣሚ ስለወደፊቱ…. የሚለው ሕልሙ እየመነመነ መጣ፡፡ አንዴ ለመጋበዝ ከጥቢ እስከበልግ ጠብቆ ያልተሳካለት ሰው፣ ስለወደፊቱ ማሰብ ዘገነነው፡፡ “ቢቀርስ?” ጠየቀ - “በጣም ይሻላል” ለራሱ ጥያቄ መልስ ያገኘ መሰለው፡፡

የመንግስት ሠራተኛው ስለወደፊቱ ማሰብን እንደዋዛ ሊያልፈው አልቻለም፡፡ “በወር ደሞዜ አንድ ራሴን አንድ ወር ማድረስ ካቃተኝ ወደፊት ዕጣ ፈንታዬ ምንድን ነው? የራሴን ቤተሰብ አልመሰርትም ማለት ነው? እስከመቼስ እንዲህ ተሁኖ ይኖራል? እስከመቼ?” ብዙ ጥያቄዎችን መጠየቅ ጀመረ፡፡ መልስ ያለው መልስ ይስጠው፡፡

1 comment: