Saturday, May 21, 2011

በድሉን ሰድጄ፥ ሃብታሙን አመጣሁ


በድሉ ‹‹ሰኒ ከዳችኝ›› እያለ ላገኘው ሰው ሁሉ የሚያወራው የቀድሞ ፍቅረኛዬ ነው፡፡ የሚገርመው ሰው ሁሉ ያምነዋል፡፡ ‹‹ድሃ ስለሆንኩ ከዳችኝ›› እያለ ነው የሚያወራው፡፡ ሴት ልጅ ከሃብታም ፍቅረኛዋ ተጣልታ ድሃ ካፈቀረች ‹‹ምን አስነክቷት ነው?›› ይባላል፤ ከድሃው ተጣልታ ሃብታም ስታፈቅር ደግሞ ‹‹በገንዘብ ቀየረችው›› ይላሉ፡፡ ሰው ማውራቱን ላያቆም የኔ ሰውነት በሐፍረት ተሸማቀቀ፡፡

በድሉን በሃብትሽ መተካቴ የሚገርማቸው ሰዎች ሁሉ ሁለቱንም እንደኔ ስለማያውቋቸው አልፈርድባቸውም፡፡ ለዚህ ነው ዛሬ ለናንተ የምነግራችሁ፡፡ ከድሮ ታሪካቸው ብጀመርላችሁ ሳይሻል አይቀርም፡፡ በድሉ ወላጆቹ ስሙን የሰጡት በአጋጣሚ እንዳይመስላችሁ፤ ሳይፈለግ በመወለዱ ‹‹በድሉ ይደግ›› ብለው ነው፡፡ እንዳሉትም በድሉ አደገ፡፡ አሁን ጎበዝ ብረት በያጅ ቢሆንም ገቢው ግን እንኳን ሰው ጨምሮበት ለራሱም ከእጅ ወዳፍ ነው፡፡

ሃብታሙ ደግሞ ገና ተፀንሶ እያለ አባቱ አምባሳደር ሆኖ በመሾሙ ለቤተሰቡ ብርቅ ነበር፡፡ አሪፍ ትምህት ቤት ተምሮ በጂኦሎጂ ዲግሪውን ከያዘ በኋላ ከአዲስ አበባ ወጥቶ እንዳይሰራ ሲባል የተከፈተለትን ሰፊ ካፌ እና ሬስቶራንት ያስተዳድራል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የማያንቀላፋ ገበያ ያለው ካፌ ብቻ ነው፤ ማን ከአፈር ጋር ይዳረቃል?

እናላችሁ፥ እኔ ሰናይት በድሉን ለገንዘብ ብዬ እንደከዳሁት ለማመን ሁሉም ሰው ይቸኩላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ሃብትሽዬ አንድም ቀን ገንዘብ ሰጥቶኝ አያውቅም፡፡ ታሪኬን ላውራላችሁ እና ራሳችሁ ፍረዱ፡፡

ከበድሉ ጋር እያለሁ ‹‹ናፍቀሽኛል ካልተገናኘን›› ብሎ ይጠራኝና ‹‹ዎክ እናድርግ›› ይለኛል፡፡ እግዚአብሔር ያሳያችሁ! ሰው እንዴት ሁለት ሰዓት ሙሉ ዎክ ያደርጋል? ይሄ ቢበቃውስ ምናለ? የአዲስ አበባ ጎዳናዎችን እንደቱሪስት ሲያስጎበኘኝ አምሽቶ ወደሰፈሬ ሲሸኘኝ፥ ጨለማ ያጠላበት የኤሌክትሪክ ምሰሶ አስደግፎ የባጥ የቆጡን ያወራልኛል፡፡ መቼም አልዋሻችሁም፡፡ በዚያ ድካም መሃል የሚያወራልኝን እንኳን ዛሬ በማግስቱም አላስታውሰው፡፡ እንደውም እዚያ የሚገትረኝ ለምን እንደሆነ ስለሚገባኝ ተሸቀዳድሜ ከንፈሬን ከንፈሩ ላይ እለጥፍለት እና እገላገላለሁ፡፡ ታዲያ እሱ ያቺን፣ ያቺን እያሰበ ፍቅሩ ልቤን ያጠፋው እየመሰለው ይኩራራል፡፡

ሃብትሽ ጋር የመጣችሁ እንደሆነ ግን፣ አቤት እንክብካቤ! ውሃ የመሰለችውን መኪናውን አምጥቶ ደሳሳ በራችን ፊት ሲያቆማት እኮ ትንፋሼ ሊቆም ነው የሚደርሰው፡፡ የእናቴ ጓደኞች እንኳን ‹‹እንዲህ ነው እንጂ እንደሰናይት ብረት መዝጊያ የሚሆነውን ማምጣት›› እያሉ ልጆቻቸውን እንደሚመክሩ ሰምቻለሁ፡፡ በድሉን እኮ እንኳን የኔ ቤተሰቦች፣ የራሱ ቤተሰቦች ራሱ የልጃቸው ባል ሆኖ ቢሄድ ኖሮ የሚወዱት አይመስለኝም፡፡ በዚያ ላይ የልብ አውቃነቱ፡፡ የሚገዛልኝ ልብሶች እላዬ ላይ የተሰፉ እንጂ ለሕዝብ ገበያ የቀረቡ አይመስሉም፡፡ ሽቶው፣ ቻፒስቲኩ፣ ሊፕስቲኩ… ጭራሸ እሱ እኔ ጋር ሲመጣ፥ መቼ ባዶ እጁን መጥቶ ያውቅና? …. ሀብትሽዬ እኮ በሻማ ብርሃን የተንቆጠቆጠ ሬስቶራንት ይወስደኝና አስተናጋጆቹ ሜኑ ሰጥተውኝ የሚበላ ሳማርጥ የገለጥኩት ሜኑ ሳይሆን የሆነ ታምር የሰፈረበት መፅሀፈ መና ይመስለኛል፡፡ ከዚያ ወደቤቱ ይወስደኝና የኳስ ሜዳ የሚያክል የስፕሪንግ አልጋው ላይ ጋደም ስል ገነት እንጂ አንድ ወንደላጤ መኝታ ቤት ውስጥ የገባሁ አይመስለኝም፡፡ ከዚያማ ምኑን ልንገራችሁ - የጨዋታው ወዙ፣ የቀልዱ ማሳቅ፣ የቁምነገሩ ሚዛን፣ የፍቅር አሰራሩ - ውይ፣ ውይ፣ ውይ፣ ውይ! ያስመንናል፡፡

ያ ስሙ እንኳን ለቁልምጫ የማይመች በድሉን ያያችሁ እንደሆነ ደግሞ፥ በስንት መከራ የቋጠራትን ሳንቲም ይዞ መጥቶ አንድ ካፌ ከወሰደኝ በኋላ የማዝዘውን ነገር ራሱ ሊነግረኝ ምንም አይቀረውም፡፡ አንድ ቀን፣ በስንት ውትወታ የሆነ ቤት ይዞኝ አድሮ - በርግጥ አልጋ ላይ እንኳን አቻ አልነበረውም - ምን ዋጋ አለው? በማግስቱ ቀሚሴ ላይ ዝልል፣ ዝልል የሚሉ ቁንጮች ይዤ ተመለስኩ፡፡

እስኪ አስቡት! ታዲያ በምን መለኪያ ነው በድሉን ከሃብትሽዬ እኩል ማፍቀር የሚቻለኝ?! ያውም እኮ ሃብትሽዬን ደረብሽብኝ ብሎ ዓይንሽን እንዳላይ ያለኝ ራሱ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ሳልነግረው ቆየሁ እንጂ ደረብኩበት አይባልም፡፡ በዚያ ላይ ሃብትሽን ያክል ሰው ብደርብበትስ አግኝቶ ነው?! ሰዉ ራሱ ይሄ መናጢ መደዴ የሚለውን ሰምቶ ‹‹በገንዘብ ቀየረችው›› እያለ ማንሾካሾኩ ነው የሚገርመው፡፡ ሾካካ ሁላ! የሌላው ሰው እንኳን ምንም አልነበረም የገረመኝ የገዛ ጓደኛዬ ነገር ነው፡፡ የኔን ዓይነት ዕድል ስላልገጠማት ቅናት አንጨርጭሯት ይሆናል እንጂ… መቼም በድሉ ከሃብትሽዬ ይሻላል ብላ አይመስለኝም - ካላበደች በቀር!

አልዋሻችሁም በድሉ ያ ብረት የሚታገልበት ጡንቻው ምን ቢፈረጥም፣ ምን መልኩ ቢያምር በሴት ጠርጥሬው አላውቅም፡፡ ሃብታሙ ግን ካፌው የገባች ሴት ሁሉ ከሱ ሌላ ወንድ የተፈጠረ አይመስላትም፡፡ እሱም መቼም ወንድ አይደል? አይፈረድበትም፤ ግን አንድ ሁለቴ ሰርቆኝ ሲባልግ ነቅቼበት ቆሽቴ እርር ብሎ እነግራታለሁ፥ ጓደኛዬ ሆዬ፣ ከትከት ብላ ስቃ ‹‹ትሻልን ሰድጄ፥ ትብስን አመጣሁ›› ብላ የአሮጊት ተረት አትተርትብኝም?

እስኪ በማን ሞት በድሉ ከሃብትሽዬ ይሻላል? ነገሯ እርር ቢያደርገኝም ዝም አላልኳትም፡፡ ‹‹በድሉን ሸኝቼ ሃብታሙን አመጣሁ›› አልኳታ፡፡ የታባቷ!!!

No comments:

Post a Comment